
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ ያላቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ እና የዴሞክራሲ ግንባታ ብስለትን የሚለካ ዋነኛ መሣሪያ ነው።
በሂደቱ ላይ የሚታይ ከፍተኛ የተሳትፎ መጠን የሕዝቡን በራስ መተማመን እና የባለቤትነት ስሜት ሲያረጋግጥ፣ ዝቅተኛ ተሳትፎ ደግሞ የፖለቲካ መገለልን ወይም በሥርዓቱ ላይ ያለን ጥርጣሬ ያሳያል። በመኾኑም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የውክልና ተሳትፎን ማሳደግ ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል።
በአማራ ክልል በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት መሳተፍ እና የሕዝብ ውክልናን ማረጋገጥ በሀገሪቱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ተገቢው ተሳትፎ እንዲኖር ለማድረግ ወሳኝ መኾኑን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የምርጫ ሂደት ላይ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሕዝቡ ጥቅሙን ለማስከበር እና ለሚወጡ ሕጎች ታማኝነት እንዲኖር ብቁ ተወካዮችን ወደ ሕግ አውጭው ምክር ቤት መላክ እንዳለበት አመላክተዋል።
ክልሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉት መቀመጫዎች ሁሉም በሕዝብ በተመረጡ ብቁ ተወካዮች ሊያዙ ይገባል። ይህም በሕዝቡ ዘንድ “ድምፄ በውሳኔው ውስጥ አለ” የሚል ሥነ-ልቦናዊ ዕምነት ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መኾኑን አስረድተዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከፓርቲ ፍላጎት ባለፈ የሕዝብን ውክልና ለማረጋገጥ ከምርጫ ቦርድ እና ከመንግሥት ጋር ተባብረው የመሥራት ኀላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ገዥው ፓርቲም ኾነ ሌሎች ተዋንያን የተለያዩ የሃሳብ አማራጮች የሚንጸባረቁበት ምክር ቤት እንዲኖር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።
የቆየው የርዕዮተ-ዓለም ፉክክር ወደ ሀገር እና ሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲቀየር የትብብር መድረኩ ሊሰፋ ይገባል ነው ያሉት።
ካለፉት ስህተቶች በመማር እና የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠል የሀገሪቱን ፖለቲካ ማሳደግ እንደሚቻል ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
