ከገለባ ወረቀት የማምረት ብቃት በተግባር !

5
‎‎ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን ከፕላስቲክ ብክለት ለማላቀቅ ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ የግብርና ተረፈ ምርቶችን ወደ ውድ የንግድ ዕቃ በመለወጥ ረገድ አንድ ተስፋ ሰጭ ፈጠራ ብቅ ብሏል።
‎ወጣት ብሩክ ነጮ የአገልግል ኢኮ ፓኬጅንግ የምርት ልማት ኀላፊ ነው። ወጣቱ ከግብርና ተረፈ ምርቶች ማለትም ከገለባ ወረቀት በማምረት የወረቀት ዘንቢልን ጨምሮ ደብተር እና መጽሐፍ እንደሚሠሩ ተናግሯል። በተጨማሪም ለኢንዱስትሪ ምርቶች ማሸጊያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ መጠን ያላቸው ካርቶኖችንም ያመርታሉ።
‎ወረቀቱን ለማምረት የስንዴ፣ የሩዝ እና የዳጉሳ ገለባ እንደሚጠቀሙ ወጣት ብሩክ ገልጾልናል። ለጣና ሐይቅ ስጋት የኾነውን እምቦጭ አረም ለማጥፋት የሚደረገውን ርብርብ ለማገዝ እምቦጭንም እንደ ግብዓት እንደሚጠቀሙት ነው የገለጸው።
‎ወረቀቱን ሲያመርቱ ለግብዓት የሚያገለግል ገለባ ከአርሶ አደሮች በወቅቱ እንደሚሠበሥቡም አጫውቶናል። ገለባው ካለው መጠን እንዲያንስ እንደሚፈጭም ነው የተናገረው።
ቀጥሎም ገለባው በኬሚካል እና በሙቀት የሚያልፍበት ሂደት አለ ነው ያለን ብሩክ። በዚህ ሂደትም ለወረቀት ሥራው የሚፈለገውን ክፍል በመለየት እና የማይፈለገውን ደግሞ ለአፈር ማዳበሪያ እንደሚውልም ገልጾልናል።
‎ለወረቀት ሥራው የሚያገለግለው ክፍል ሌሎች የኬሚካል ሂደቶችን አልፎ ወደ ማሽን ገብቶ ወረቀቱ ይሠራል ብሏል። ከተሠራ በኋላም በጸሐይ ሙቀት እንደሚደርቅ ነው የገለጸው።
‎ሥራውን የጀመሩት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ኾነው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በነበረው የቢዝነስ ኢንኩቬሽን ጥሪ አመልክተው እና በፈጠራ ማዕከሉ ገብተው እንደኾነም አጫውቶናል።
የፈጠራ ሥራቸውን ወደ ምርት ለመቀየር እና በላበራቶሪ እና ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ለማምጣት ዓመታትን ወስዶባቸዋል። ሥራውን ከጀመሩ ከአምስት ዓመት በላይ መኾኑንም አንስቷል።
‎ከመነሻው በእጅ ሠርቶ በማምረት እና በትንሹ ከመሸጥ ጀምረው አሁን ላይ በማሽን አምርቶ ወደ መሸጥ እንደገቡም ገልጾልናል።
‎የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ክህሎት መምሪያ ሥራቸውን በማየት የማምረቻ ቦታ እገዛ እንዳደረገላቸው ነው የገለጸው። አሁን ላይ ለ22 ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም አንስቷል።
‎በዚህ የፈጠራ ሥራቸውም ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳሸነፉ ነው የገለጸው።
‎አሁን በሀገሪቱ የፕላስቲክ ምርቶች መከልከሉን ተከትሎ የወረቀት ዘንቢል በሰፊው እያመረቱ መኾኑን አጫውቶናል። ምርቶችን በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንልካለን ነው ያለው ወጣቱ።
በቀጣይ የመማሪያ ደብተሮችን በማምረት እና ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አቅደው እየሠሩ መኾኑንም ገልጿል።
‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleምርጫ ዜጎች መብታቸውን እንዲለማመዱ ከማገዙም ባለፈ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ነው።
Next articleምርጫው ሕዝቡ ብቁ እና በቂ ተወካዮች እንዲኖሩት የሚያደርግ በመኾኑ ልዩ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል።