
ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ላይ ሰፊ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት በስዊድን ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ስታፋን ሊንድበርግ እንደሚሉት ተደጋጋሚ ምርጫዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው።
በዓለም አቀፍ የሳይንሳዊ ምርምሮች ማጋሪያ ድረ-ገጽ የተጋራው ጽሑፋቸው እንደሚጠቁመው ሊንድበርግ ምርጫን እንደ ተራ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሳይኾን የፖለቲካ ምህዳሩን ደረጃ በደረጃ የሚቀይር የለውጥ ሞተር አድርገው ይመለከቱታል።
ምርጫ ዜጎች መብታቸውን እንዲለማመዱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን እንዲያደራጁ እና ሥልጣን በሕግ አግባብ ብቻ እንዲያዝ ዕድል በመስጠት ረገድ ለዴሞክራሲያዊ ልምምድ ጉልህ አበርክቶ ይወጣል ነው ያሉት።
በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የሚታዩ አስከፊ ምርጫዎች የዚህን ጽንሰ-ሃሳብ ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከቱት ቢጠቁሙም፣ ተደጋጋሚ ምርጫዎች ግን የዴሞክራሲ ተስፋን እንደሚያለመልሙ በጽሑፋቸው አስፍረዋል።
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፒፓ ኖሪስ (ዶ.ር) የአንድ ሀገር ምርጫ ተአማኒነት እንዲኖረው የሂደቱ ፍትሐዊነት፣ ጠንካራ የአሥተዳደር አቅም እና ክፍት የመረጃ አውታሮች መኖር ወሳኝ መኾናቸውን ይሞግታሉ።
ዜጎች የምርጫ ሂደት ታማኝነት እንደጎደለው ወይም በማጭበርበር የተሞላ እንደኾነ ካሰቡ በቀጥታ በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያላቸውን ዕምነት እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ሕጋዊነት ያዳክመዋል ብለዋል።
ምርጫ መካሄዱ ብቻውን በቂ እንዳልኾነ እና የሂደቱ ታማኝነት መጓደል ለዴሞክራሲ መላሸቅ ዋነኛ ምክንያት እንደሚኾንም ምሁሯ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
