
ባሕር ዳር: ግንቦት7/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላስቲክ ምርት ለረጅም ጊዜ የማይበሰብስ በመኾኑ በብዝኀ ሕይወት፣ በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያስከትላል።
በተለይ የአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ፕላስቲኮች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ከፍተኛ ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ በሀገር ውስጥ እንዳይመረቱ እና በንግድ ዝውውር ውስጥ እንዳይካተቱ የሚከለክል አዋጅ 1383/2017 ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።
አዋጁን መሠረት በማድረግ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም እንደማይቻልም ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ይኹን እንጅ አኹን ላይ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀሚያ ጊዜ “ተራዝሟል” የሚል ወሬ እየተናፈሰ ይገኛል፤ በግብይትም በአገልግሎትም ላይ እየዋለ ነው?
#ክልከላው ተራዘመ እንዴ?
በአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት፣ ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር መዝገቡ ዳኘው የተራዘመ ክልከላ የለም አሉን።
#ታዲያ አኹን ፕላስቲኮች አገልግሎት እየሠጡ አይደለም? እስካኹን በአደረጃጀት እና በመመሪያ ዝግጅት ሥራ ምክንያት ወደ ተሟላ የሕግ ማስከበር ሥራ አልተገባም ብለዋል ዳይሬክተሩ።
የመዋቅር ሥራውን በፍጥነት በማጠናቀቅ በመጭው የክረምት ወራት ጀምሮ ወደ ሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ምርቱን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን፣ በጅምላ ወይም በችርቻሮ የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችን፣ እንዲኹም ፕላስቲኮችን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ተጠያቂ እንደሚኾኑም ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
