“ለሀገር ሰላም እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት በጋራ እንቁም” አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ

3
🕊️🗳️ባሕር ዳር: ግንቦት 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ፓርቲዎች የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ። በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ አንዱ ነው።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ(አዴኃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ ፓርቲያቸው ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ በማይቻልበት ወቅት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱን ወደ ኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ግን ፓርቲያቸው ሰላማዊ የትግል አማራጭን መርጦ በምርጫ ሂደት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለሁለተኛ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል። በሂደቱም በርካታ ልምዶች የተገኘበት ነው ብለዋል።
ዴሞክራሲ ሂደት ነው የሚሉት አቶ ተስፋሁን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ የመሥራት ባሕል እየዳበረ መምጣቱንም እንደ ስኬት ያነሳሉ። በሀገር ጉዳይ በጋራ መቆም እና ለብሔራዊ ጥቅም አብሮ መሰለፍን አይተንበታል ነው ያሉት፡፡
እንደ ሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ አዴኃንም ለምርጫው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል። በአየር ሰዓት ድልድሉ እና በፓርቲው አደረጃጀት የፓርቲውን አማራጭ ፕሮግራሙን ለሕዝቡ ማቅረቡን ጠቁመዋል።
በምረጫ ቅስቀሳ ወቅት የሰለጠነ አካሄድን በመከተል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ም አሳስበዋል። ሕግን እና መመሪያን ተከትሎ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ሁሉም ፓርቲ ለሀገር ሰላም እና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት በጋራ መቆም እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ ይፈልጋል ያሉት አቶ ተስፋሁን በምርጫው እለትም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሚፈልጉትን ፓርቲ በካርዳቸው እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሙዚየሞች አንዱ የሌላውን ባሕል፣ ወግ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲማር የሚያደርጉ የምርምር ማዕከላት ናቸው።
Next articleበአማራ ክልል ስኬታማ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የፓለቲካ ምሕዳር ተፈጥሯል።