ሙዚየሞች አንዱ የሌላውን ባሕል፣ ወግ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲማር የሚያደርጉ የምርምር ማዕከላት ናቸው።

5

 

​አዲስ አበባ፡ ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የሙዚየም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ፣ በሀገር ደረጃ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ግንቦት 10/2018 ዓ.ም እንደሚከበር የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ጋር በመተባበር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ በቀለ (ዶ.ር) እንደገለጹት በዓሉ “ሙዚየሞች የተከፈለውን ዓለም ያስተሳስራሉ” በሚል መሪ መልዕክት መከበሩ ዓለም በፖለቲካ በተከፋፈለችበት ወቅት የጋራ ታሪክን ለመገንባት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

ሙዚየሞች ማኅበራዊ ሚዲያ እያራራቀው ያለውን ትውልድ ለማቀራረብ የሚረዱ ተቋማት መኾናቸውን ጠቅሰዋል። በዕለቱ የዓድዋ ሙዚየም ለጉብኝት ክፍት መኾኑን ገልጸው ሁሉም ሙዚየሙን እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ሙዚየሞች የተከፋፈለውን ዓለም አንድ ያደርጋሉ የሚለው መሪ መልዕክት ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንደሚጣጣም እና የዓድዋ ድልም ኢትዮጵያውያንን አንድ ያደረገ ትልቅ እሴት መኾኑን ገልጸዋል።

ሙዚየሞች ያለፈውን አስተሳሰብ በመተው ማኅበረሰቡ አንዱ የሌላውን ባሕል፣ ወግ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲማር የሚያደርጉ የምርምር ማዕከላት መኾናቸውንም አክለዋል።

በተጨማሪም ሙዚየሞች ከቴክኖሎጂ ጋር በመቀናጀት ሕዝቡ ባለበት ኾኖ ታሪኩን ማወቅ እና መረዳት የሚያስችል ዕድል መፈጠር እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አሳስበዋል። ይህም በዓሉን ለማክበር ከተቀመጡ ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ መኾኑ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን

#አሚኮ #ዜና #ሙዚየም #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከእውነት የራቁ መረጃዎችን እያሰራጩ የሚገኙ አካላትን አላማ መገንዘብ ያስፈልጋል።