
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጽንፈኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚሸረሸር የሕዝቦች አብሮነት እንደማይኖር የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አስታውቋል።
ጽንፈኞች በሚነዙት የሀሰት ወሬ የሚደፈርስ ሰላምም አይኖርም ብሏል ተቋሙ።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሔኖክ ሙሉነህ የክልሉ መንግሥት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሠሩ ተግባራት ፍትሐዊነትን ያረጋገጡ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ሕዝቡም የክልሉ መንግሥት እያስመዘገባቸው በሚገኙ ስኬቶች ላይ እራሱ እየመሰከረ ባለበት ወቅት አንዳንድ እኛ እናውቅልሃለን’ የሚሉ ጽንፈኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸውን በመንዛት ለማደናገር እየተውተረተሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
መቃወምን ብቻ እንጀራቸው ያደረጉ እነዚህ ጽንፈኞች የሕዝብን ሳይኾን የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚፈልጉ አካላት መኾናቸውን ሕዝቡ በሚገባ እንደተገነዘበ ሊያውቁት ይገባል ብለዋል።
ስለኾነም ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ በማስመሰል በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ የጥላቻ እና “ከእውነት የራቁ መረጃዎችን እያሠራጩ የሚገኙ አካላትን አላማ መገንዘብ” እና ለሕግ እንዲቀርቡ የተለመደ ትብብርን ማድረግ እንደሚገባም ማንሳታቸውን ከክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
#አሚኮ #ኢትዮጵያ #ሐረር
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
