📱የኢንተርኔት ባንኪንግ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ አለው።

2

 

​ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሕር ዳር ዲስትሪክት እና የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በኢንተርኔት ባንኪንግ አጠቃቀም ዙሪያ አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

🤝በፊርማ መርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን እንደገለጹት ስምምነቱ የፋይናንስ ሥርዓትን ይበልጥ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያግዝ ነው።

የመንግሥት የገንዘብ ዝውውርን ባንክ መሄድ ሳያስፈልግ በኢንተርኔት በማከናወን ጊዜን እና ወጭን ለመቆጠብ እንደሚያስችል አስረድተዋል። ዜጎችም ባሉበት ኾነው በቀላሉ ክፍያ እንዲፈጽሙ ያግዛል ነው ያሉት።

የመንግሥትን የወጭ እና ገቢ አሥተዳደር በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል። እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም አንስተዋል።

የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ከባለድርሻ አካላት፣ ከሴክተር መሥሪያ ቤቶች እና ከባንኩ የሚጠበቁ ኀላፊነቶችን በግልጽ በመለየት በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ኀላፊ ደመወዝ ባልቤ እንዳሉት የዲጂታል የኢንተርኔት ባንኪንግ ሥርዓት ገንዘብን ከተለያዩ አደጋዎች በመጠበቅ ለማሥተዳደር ትልቅ ፋይዳ አለው። አሠራሩ በፌዴራል ተቋማት ላይ ሢሠራበት መቆየቱንም አንስተዋል።

ሥርዓቱ የተቋማት ኀላፊዎች እና የሂሳብ ሠራተኞች ቢሮ ላይ ባይገኙም በማንኛውም ቦታ ኾነው ግብይቶችን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በስምምነቱ መሠረት ከኢንተርኔት ባንኪንግ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን እና ፋሲሊቲዎችን በማሟላት ከተቋማት ጋር ለመሥራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

#አሚኮ #ዲጂታል2030 #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🌾”ብልጽግና ሀገሪቱን ከተረጅነት ወደ ረጅነት እያሸጋገረ ያለ ፓርቲ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleፕሬዝዳንት ትራምፕ በቻይና ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ እየጎበኙ ነው።