🌾”ብልጽግና ሀገሪቱን ከተረጅነት ወደ ረጅነት እያሸጋገረ ያለ ፓርቲ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

2

 

​ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመቄት ቁጥር አንድ የምርጫ ክልል በፍላቂት ገረገራ ከተማ አሥተዳደር በመገኘት የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል።

የሰሜን ወሎ አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ብልጽግና የፖለቲካ አካታችነትን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በሕዝብ ፈቃድ የተመሠረተ ፓርቲ መኾኑን ተናግረዋል።

ብልጽግና የምግብ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እየኾነ የሚገኝ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በመቄት ወረዳ እና በፍላቂት ገረገራ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች በብልጽግና ፓርቲ ምላሽ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ የመቄት እና አካባቢው ሕዝብ ባለፈው ምርጫ ብልጽግናን በመምረጡ አመሥግነዋል። በቀጣዩ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግናን እንዲመርጡም ጠይቀዋል።

ዜጎች በሁሉም አካባቢ ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ፣ ከድህነት እንዲላቀቁ፣ ሀገር የባሕር በር ባለቤት እና ሕዝቡም የወደብ ተጠቃሚ እንዲኾን፣ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እና ጽዱ እንዲኾኑ ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ ይገባል ነው ያሉት።

በከተማዋ የኮሪደር ልማት እንዲሠራ ዛሬ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር መካሄዱንም ተናግረዋል። ብልጽግናን መምረጥ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው ብለዋል።

በወረዳው የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ብልጽግና ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን ተጠቃሚነት እንድታረጋግጥ ያደረገ ፓርቲ ነው ብለዋል።

የዓባይን ወንዝ ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም ሢሠሩ የነበሩትን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ክብር በማስጠበቅ በታሪክ እንዲቀመጥ አድርጓል ነው ያሉት።

ነዋሪዎቹ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እያደረጉት ስላለው ጥረት አመሥግነው አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ዓለማቀፋዊ ራዕይ ያለው፣ ኢትዮጵያ በዓለም እና በአፍሪካ ልዕለ ኀያል እንድትኾን የሚሠራ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ ከተረጅነት ወደ ረጅነት በመሸጋገር የሀገርን ክብር ከፍ እያደረገ ያለ ፓርቲ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

የብልጽግና ከፍታ የሚያስፈራቸው ኀይሎች የሀገርን ሰላም ለመበጥበጥ የሚሠሩ መኾናቸውን አንስተው እንቅስቃሴያቸውን በማስቆም የሀገርን ሰላም ለማጽናት ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱንም ገልጸዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ለምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት እና ዕድገት ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል።

ብልጽግና ኢትዮጵያ በዓለም ኢኮኖሚ ተፎካካሪ እንድትኾን እየሠራ በመኾኑ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ብልጽግናን ምረጡ ብለዋል።

ምልክታችን የስንዴ ነዶ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንደ ስንዴ ነዶ አንድ በመኾን ኢትዮጵያን እናሻግራለን ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

#አሚኮ #ዜናምርጫ #ሰሜንወሎ #አማራክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብልጽግና ፓርቲ በተግባር የታዩ የልማት ለውጦችን አስመዝግቧል።
Next article📱የኢንተርኔት ባንኪንግ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ አለው።