
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት የሚቋቋምበት እና ዕኩልነት የሚረጋገጥበት ሥርዓት ነው።
ዜጎች የሀገራቸውን ፍቅር የሚገልጹበት እና ዴሞክራሲን የሚለማመዱበት ነጻ ሜዳም ነው። ይህ የሚኾነው ግን በያገባኛል መንፈስ ሁሉም መሳተፍ ሲችል ነው።
የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ፕሬዝዳንት መሪጌታ ብሩህ ዘላለም ምርጫ ላይ በንቃት መሳተፍ ሀገር ላይ የመወሰን ዕድልን የመጠቀም ጉዳይ ነው ብለዋል። ሰላማዊ ምርጫ ላይ በንቃት መሳተፍ አለብን ነው ያሉት።
ምርጫው ሰላማዊ እንዲኾን ሁሉም ዜጋ ድርሻ አለበት ያሉት መሪጌታ ብሩህ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ኀላፊነት ደግሞ እጥፍ ድርብ ነው ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ስለ ሀገር መጸለይ እና ትውልዱን መክሮ መመለስ ዋና ጉዳያቸው እንደኾነም ገልጸዋል።
ትውልዱ ሁልጊዜም በሀገሩ ጉዳይ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን ምክር ስንቅ ማድረግ አለበት ነው ያሉት። ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
በዚህ ወቅት የሰከነ አዕምሮን መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል። “አባቶች መካሪ፤ ልጆች ተመካሪ ኾነን ምርጫውን በስኬት ማጠናቀቅ አለብን” ነው ያሉት።
በዕድሜየ ሁሉ ካስተዋልኳቸው መልካም ነገሮች መካከል የሀገር ሰላም ሁልጊዜም መቅደም እንዳለበት ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ምክትል ሠብሣቢ ይመር ሰይድ ናቸው።
የምናልማትን ሀገር ለማስቀጠል ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ አለብን፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መሥራት አለብን ብለዋል።
ለምርጫው ሰላማዊነትም እንደ ሀገር ሽማግሌ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
#አሚኮ_ዲጂታል_ሚዲያ #ምርጫ #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
