
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለምታካሂደው ምርጫ የትውልድ ቀራጮች የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነው።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ መምህራን በምርጫ ካርድ የሚፈልጉትን መምረጥ ነገ “ባልመረጥኩት እየተመራሁ ነው” ከሚል ታሪካዊ ጸጸት እንደሚያድን ተናግረዋል።
ለዚህም መፍትሔው ለምርጫ ካርድ ትኩረት መስጠት እና በምርጫውም ንቁ ተሳታፊ መኾን እንደኾነ ገልጸዋል። መምህራን የተማረ እና የታነጸ የሰው ኃይል በማፍራት ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላም እና ለልማት የሚወጡት ኀላፊነት መሠረታዊ መኾኑን የተናገሩት መምህር ዓለም ገብረ ጻድቅ ናቸው።
የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን እና በምርጫው ቀን ለፈለጉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደኾኑም ተናግረዋል። መምህራን ዜጎችን በአግባቡ በመቅረጽ ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል።
ሌላኛው መምህር ማስረሻ ተባባል በመጭው ሀገራዊ ምርጫ የመምህራን ሚና እና ተሳትፎ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል። ምሁራን በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ካላቸው ልምድ እና ዕውቀት በመነሳት ንቁ ተሳታፊ መኾን እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል።
ሀገር በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እና “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንድትመራ መምህራን ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም” ጠቁመዋል።
በተለይም ከተማሪዎች ጋር ያላቸው ቀረቤታ፤ በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ደረጃ ሰላም እና መግባባት እንዲሰፍን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
መምህራን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን አማራጭ አጀንዳዎች በመመዘን ይበጀኛል የሚሉትን በካርዳቸው እንዲወስኑም አሳስበዋል።
ድምጼ ዋጋ አለው በሚል ባለፉት ዓመታት እንዳደረጉት ሁሉ ዘንድሮም ይመራኛል ለሚሉት ድምጻቸውን በመስጠት ወሳኝነታቸውን ለማረጋገጥ የምርጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቁ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) መምህራን ማኅበረሰቡን የማስተማር እና የማንቃት ቀዳሚ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ በርካታ መምህራን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል። መምህራን በምርጫው ቀን የምርጫ ሕጉን መሠረት በማድረግ ለሚፈልጉት አካል ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። የዜግነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
