
ባሕርዳር፡ ግንቦት 06/2018ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እናቶች ማኅበር ሀገራዊ ሰላምን፣ እርቅን እና አንድነትን ለማጽናት በግንባር ቀደምትነት የሚንቀሳቀሱ የሰላም አምባሳደሮችን የያዘ ነው። ማኅበሩ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የቆዩ የሰላም እሴቶችን ለማነቃቃት በትጋት ይሠራል።
የአማራ ክልል የሰላም እናቶች ማኅበር አባላትም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሠርካለም ገዛኸኝ እንደገለጹት እናቶች ሰላምን በማጽናት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።
እናቶች ልጆቻቸው ወደማይፈለጉ ድርጊቶች እንዳይገቡ የመከላከል እና ወጣቱ ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲይዝ የማድረግ ሥራን በቁርጠኝነት እያከናወኑ ይገኛሉ።
“ሰላም ከቤተሰብ ይጀምራል” ያሉት ወይዘሮ ሠርካለም፤ ልጆች ሲያድጉ እናቶቻቸውን በአርዓያነት እንዲከተሉ እና ግጭቶችን በውይይት የመፍታት ባሕል እንዲያዳብሩ ሁሉም እናቶች የሰላም አምባሳደር መኾን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሌላኛዋ የማኅበሩ አባል እና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የግምጃ ቤት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አልጋነሽ አስፋው በበኩላቸው እናቶች ግንባር ቀደም በመኾን ሰላምን የመስበክ እና ግጭቶችን የማረጋጋት ሥራ እያከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም ልጆችን፣ ወንድሞችን እና ጎረቤቶችን በማስተማር የማኅበረሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ ተደራጅተው እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የሰላም እናቶቹ የምርጫ ካርድ በማውጣት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በሰላማዊ ምርጫ ዘላቂ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ የጠቀሱት እናቶቹ ሌሎችም የእናትነት እና የእህትነት ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
እናቶች በየአካባቢያቸው የሰላም አብሳሪ፣ የልማት አጋር እና የአብሮነት ተምሳሌት በመኾን ለሀገር ግንባታ ግንባር ቀደም ኾነው ሊሠሩ እንደሚገባም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
