
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ሂደት ፍትሐዊ የመገናኛ ብዙኀን አጠቃቀም መኖር ለነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ ምርጫ መሠረት ነው፡፡ መገናኛ ብዙኀን ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ ሀሳብ ለመራጩ ሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ሕዝቡ የሚፈልገውን ፓርቲ በሚገባ አውቆ እንዲመርጥ ያስችላል።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተደረገው የሚዲያ ድልድል እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠው የአየር ሰዓት የሚበረታታ መኾኑን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ጸጋዬ መገናኛ ብዙኀን አማራጭ ሀሳብ ላላቸው ፓርቲዎች በፍትሐዊነት ክፍት እንዲኾኑ ያስፈልጋል። ይህም መራጩ ሕዝብ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስን ዕድል ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡
በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ከገዢው ፓርቲ ብልጽግና ጋር ተመሳሳይ የአየር ሰዓት ድልድል መኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮች በአግባቡ እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት። ለአብነትም በአሚኮ የተደረጉ የምርጫ ክርክሮችን አንስተዋል።
ፓርቲያቸውም ያገኘውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም አማራጭ ፖሊሲዎቹን ለሕዝብ በማስተዋወቅ እየተጠቀመበት መኾኑን ተናግረዋል። ለቀጣይም ትልቅ ልምድ የሚወሰድበት እንደኾነም ነው የሚገልጹት።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል አዲሱ ጉልላት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተፈቀደው የሚዲያ አጠቃቀም ቀደም ሲል ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሰጠው ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አንዱ ማሳያ መኾኑንም ያነሳሉ።
ለሁሉም ፓርቲዎች ዕኩል የሚዲያ ዕድል መፈጠሩ ሕዝቡ አማራጮችን በሚገባ አውቆ እንዲወስን ተገቢውን ድምጽ እንዲሰጥ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ፓርቲያቸውም በተመቻቸው የሚዲያ ድልድል መሠረት አማራጭ ፖሊሲዎችን በንቃት ለሕዝቡ በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
