
አዲስ አበባ፡ ግንቦት 06/2018ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በርክክብ መርሐግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የአጼ ቴዎድሮስ ንብረት የነበሩ ቅርሶች ተሰርቀው ከሀገር ቢወጡም ከ158 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ለዲፕሎማሲው ስኬት ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
በተለይም የፊታችን ሰኞ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ የሙዚየሞች ቀን ምክንያት በማድረግ ቅርሶቹን ማምጣት መቻሉ ለሀገር ትልቅ ኩራት መኾኑንም ተናግረዋል።
የአጼ ቴዎድሮስን ቅርሶች ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው ታላቅ ደስታ እንደሚሰማቸው የገለጹት ደግሞ በእንግሊዝ የኪንግሥ ኦን ሮያል ሬጅመንት ሙዚየም ሊቀመንበር ሮቢን ጃክሰን (ዶ.ር) ናቸው። ለዚህ ተግባር መሳካትም ከእንግሊዝ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልባዊ ምሥጋና መቅረቡን ዶክተር ሮቢን ተናግረዋል።
አሁን ወደ ሀገር የተመለሱት ሦሥት ዋና ዋና ቅርሶች መኾናቸውን ያስረዱት የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ.ር) በበኩላቸው ቅርሶቹ የወርቅ አምባር፣ ለረጅም ጊዜ በእንግሊዝ ሙዚየሞች የቆየ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳላ እና አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በነበሩበት ወቅት ይለብሱት የነበረው የሸማ ልብስ ቁራጭ መኾኑን ተናግረዋል።
በዚሁ ርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት እነዚህ ቅርሶች መመለሳቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረው በቀጣይም ሌሎች ቅርሶች እንዲመለሱ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
እነዚህን ቅርሶች ለማስመለስ ለተረባረቡ ሁሉ ምሥጋና የቀረበ ሲኾን እነዚህ ቅርሶች መመለሳቸው በቀጣይ ሌሎች በውጭ ሀገራት የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ ትልቅ በር እንደሚከፍት ታምኖበታል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
