
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2018 ዓ.ሜ (አሚኮ) “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የብልፅግና ፓርቲ አባላት እና የመንግሥት ሠራተኞች መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦችን የተመለከተ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ ብልፅግና ፓርቲን ወክለው በባህርዳር ከተማ የሚወዳደሩ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት ዕጩዎች ትውውቅም ተደርጓል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ ኾኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም በሀገራዊ ስሜት ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ለውጡ በኃላ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በድል እየተሻገረች በርካታ ልማታዊ ሥራዎችን በተግባር ያሳካች ስለመኾኗ ጠቅሰዋል። የውጭ ባዕዳ እና የውስጥ ባንዳ ቢገጥማትም ከልማት ጉዞዋ ግን አላስቆሟትም ነው ያሉት። ተግዳሮቶችን ሁሉ በጽናት በማለፍ አሁን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ከምንጊዜውም በላይ ለማጽናት በምርጫ ዋዜማ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምሁራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሀገራዊ ምርጫ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማሳደግ ተጨማሪ መሠረት በመሆኑ ምሁራን የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንችአምላክ ገብረ ማርያም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ እና ከምንጊዜውም በላይ የሀገር ዴሞክራሲያዊ መሠረት የሚጣልበት መኾኑን ተናግረዋል። በምርጫው ውቢቷ ባሕር ዳር ከተማን ወክለው የሚወዳደሩ እንቁ የሀገር ልጆች መኖራቸውን ጠቅሰው ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ አካሄድን የተከተለ እንዲኾን እየተሠራ ስለመኾኑ አረጋግጠዋል።
የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎችም የሀሳብ የበላይነትን አጥብቆ በመያዝ በምርጫው ላይ ንቁ ተሳታፊ መኾን እንዳለባቸውም ተናግረዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫው ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚጠበቅባቸውም ኀላፊዋ አስገንዝበዋል።
የምርጫው ሂደት ሀገረ መንግሥት ከመመሥረትም በተጨማሪ ለስኬታማነቱ በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ሠራኞችን ያስተሳሠረ እና ለጋራ ሥራ ያነሳሳ እንደኾነም ተናግረዋል። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ እና ከተማ አሥተዳደሮች ድረስ ያሉ መሪዎች እና የፓርቲው አባላት በቅንጅት የሠሩበት እና ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ጉዞ በቁርጠኝነት የሚደረገውን ርብርብ በተግባር ያስመሰከሩበት ነበር ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ኀላፊ ኀይሌ አበበ በበኩላቸው ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ድጋፍ ሰለፉ ድረስ ባለው ሂደት የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ለሀገራዊ ምርጫው መሳካት እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተግባር አሳይቷል ብለዋል። በቀጣይም ሀገራዊ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረገው ውይይት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ምሁራን በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ችግሮችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
