
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ተወያይተው የጋራ ምክር ቤቱ መሪዎች መግለጫ ሰጥተዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከፓርቲዎች ጋር ገንቢ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
ምርጫው ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
“ሀገር ከፓርቲ በላይ ነው” ያሉት ሰብሳቢው ይህንን በውል በመገንዘብ በቅስቀሳ ወቅት ወደ ግጭት እንዳያስገባ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ አቋም ተወስዷልም ነው ያሉት።
መራጮች በምርጫው ዕለት በነቂስ ወጥተው እንዲመርጡ ማድረግ ላይም ግንዛቤ መወሰዱን አብራርተዋል።
በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በጋራ ምክር ቤቱ በውይይት እና በሠለጠነ መንገድ መፍታት እንደሚገባም የጋራ ተደርጓል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሠብሣቢ መስፍ አበጀ (ዶ.ር) በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ ፓርቲዎቹ በጋራ በመሥራት ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በተለይም በሰላም ጉዳይ፣ በእጩዎች ምዝገባ እና በመራጮች ምዝገባ በጋራ በተሠራው ተግባር ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲዎች ተሳትፎ፣ በምርጫው አስፈላጊነት፤ የፖለቲካ ምህዳሩን በመጠቀም እና በሰላም ጉዳዮች ውጤታማ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።
ምርጫው የዘላቂ ሰላም ዋስትና መኾኑን የጋራ ድምዳሜ ላይ መደረሱንም አንስተዋል። ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እና ምርጫው ስኬታማ እንዲኾን የጋራ ምክር ቤቱ የሚጠበቅበትን በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
