“ጋሸና እና አካባቢው ከብልጽግና ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ይኾናል” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

8
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና ከተማ መቄት ቁጥር ሁለት የምርጫ ክልል ላይ የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል።
የጋሸና ከተማ አሥተዳዳር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጸጋ ውቤ የብልጽግና ፓርቲ ጋሸና በከተማ አሥተዳደርነት እንድትመራ፣ ከተማዋን ከተለያዩ ወረዳዎች እና ዞኖች የሚያገናኙ የመንገድ ግንባታዎች በማከናወን ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የመብራት ኀይል ማከፋፈያ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ልማት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት ከተማዋ የልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትኾን አድርጎል ነው ያሉት። የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ሀገርን ለማልማት የማዳበሪያ፣ የነዳጅ እና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ የሚገኝ ፓርቲ መኾኑንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድህነት በማላቀቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትኾን በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል። በዞኑ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መኾኑን ጠቁመው ብልጽግናን በመምረጥ ልማቶች እንዲቀጥሉ እና ጋሸና የልማት ተጠቃሚ እንድትኾን ልታደርጉ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ጋሸና በብልጽግና ፓርቲ የልማት እቅዶች ትግበራ ትለማለች ብለዋል።
ልማት ያለ ሰላም አይመጣም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ታጣቂዎችን በመምከር እና የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ በማድረግ የከተማዋ ልማት እንዲስፋፋ ልትሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
ብልጽግናን ችግሮች እንደማያስቆሙት ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳደሩ ኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ሕዝቧን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾን ለማስቻል፣ ድህነት እና ኋላ ቀርነትን ለማስቀረት ብሎም ሕዝባዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ከብልጽግና ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጋሸና ተጠቃሚ እንደምትኾንም ተናግረዋል። በሕዝብ መካከል የመለያየት ቁርሾ የሚዘሩትን በመቃወም የጋራ ትርክትን ልትፈጥሩ ይገባልም ነው ያሉት።
ብልጽግና ኹሉንም አስተሳስሮ የሚይዝ በመኾኑ ብልጽግናን ልትመርጡ ይገባል ብለዋል። ብልጽግናን በመምረጥ አንድ በመኾን ሀገራችንን እናለማለን ብለዋል።
የጋሸና እና ዋድላን ሕዝብ በምርጫ ምዝገባ ላሳዩት ተነሳሽነት አመሥግነው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ብልጽግናን በመምረጥ ልማትን እንዲያስቀጥሉም አሳስበዋል።
የስንዴ ነዶን በመምረጥ የሀገርን ሉዓላዊነት እንድታረጋግጡ እጠይቃለሁም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተወያዩ።
Next articleየሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ የግል ዳታን ከመጠበቅ ይጀምራል።