
ባሕርዳር፡ ግንቦት 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ለተደራጁ ማኅበራት ዕውቅና ሰጥቷል። የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ቀደም ሲል የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ከተመዘገቡ 894 ማኅበሮች መካከል 780 ለሚኾኑት ዕውቅና እየተሠጠ መኾኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ዕውቅና ከተሰጣቸው ማኅበራት ውጭ ያሉት ቀሪዎቹ ማኅበራት ለቅድመ ቁጠባ ወደ ባንኮች ዝርዝራቸው ያልተላኩ ማኅበራት እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በቅሬታ ሂደት ጉዳያቸው እየታየላቸው ያሉ ማኅበራት ናቸው። ከዚህ ዕውቅና በኋላ በሚኖር ቅርብ በሚባል ጊዜ ውስጥ ዕውቅና ያገኛሉ ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት በነበረ የቦታ ፈላጊዎች ማደራጀት ሥራ መጓተቶች ነበሩ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማዋ ይህን የተጓተተ አሠራር በመቅረፍ በዚህ ዙር ደግሞ በ2017 ዓ.ም የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ተመዝግበው ሲጠባበቁ የነበሩ ቦታ ፈላጊዎችን አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።
ለ25ሺህ ቤት መሥሪያ ቦታ ፈላጊዎች የሚኾን ቦታ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። በዚህም የአርሶአደር ልጆችም ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ገልጸዋል። ለእያንዳንዱ ግለሰብ 150 ካሬ ቦታ ለመስጠት እንደተወሰነም ጠቅሰዋል።
ሌሎች የከተማ ነዋሪዎችንም የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ ምዝገባ በቅርብ ይከወናልም ብለዋል።
የመሬት ካሳም ውሳኔ አግኝቷል፤ የካሳ ክፍያው እንደተጠናቀቀም በግንቦት ወር አጋማሽ የቦታ ርክክብ ይደረጋል ነው ያሉት። በዚህ ዙር በተለይም ደግሞ የኑሮ ውድነቱ እየፈተናቸው ካሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በቤት መሥሪያ ቦታ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማድረግ ጥረት እንደተደረገም ጠቅሰዋል።
ይህን ቦታ መውሰድ ብቻ ሳይኾን በመገንባት የችግራቸው መፍትሔ እንዲያደርጉም የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
#አሚኮ #ዜና #የቤትልማት #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
