
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ ላይ ትገኛለች። ለዚህም ባለፉት ጊዜያት ስድስት ያህል ምርጫዎችን ማድረጓ ማሳያዎች ናቸው።
አሁን ደግሞ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን እየሠራች ነው። በዚህ ሂደት ታዲያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ልምምዱን በተግባር እያየም ይገኛል።
ምርጫ መንግሥት ለመመሥረት እና ሀገር ለማቆም ወሳኝ ነው ሲባል ቀላል ነገር አይደለም ያሉት በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ምስክር ከተማ ናቸው። ይህን ወሳኝ ሂደት በየጊዜው እየተለማመዱ ለሀገር መቆም እና መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት መመሥረት ሀገርን ከመበተን እና ከጥፋት መታደግ ነው የሚሉት መምህሩ ይህ ሂደት ከልማቶች ሁሉ የበለጠው ጉዳይ በመኾኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ባይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲን እየተለማመደ እየመጣ ነው ያሉት መምህሩ ይህ ሂደት ግን ወደ ኋላ መመለስ የለበትም ብለዋል።
አንዳንድ ሰዎች ችግሮች እያሉ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል ሲሉ እሰማለው ያሉት መምህሩ ይሁን እንጅ ምርጫ በችግሮችም ውስጥ ቢኾን አልፎ ችግርን የሚያስወግድ መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በጥቃቅን ችግሮች ተጠምዶ ምርጫ አለማከናወን ትንሹን ችግር ወደ ገዘፈ ችግር መቀየር እንደኾነም አስረድተዋል። ምርጫ ማከናወን የመሠልጠን ምልክት እንደኾነም ጠቁመዋል። ምርጫ የሚያከናውን ማኅበረሰብ በጥቂቱም ቢኾን ተጠያቂነትን ለማስፈን የተዘጋጀ ሀገር መኾኑን ያሳያልም ነው ያሉት።
በዓለም ላይ ጥሩ ምርጫ እና ሥልጡን ሕዝብ ያላቸው ሀገራት ለዕድገታቸው ቁልፍ እንደኾነላቸው ታይቷል ነው ያሉት።
በአፍሪካም በምርጫ ምክንያት ሀገርን የሚጎዱ ነገሮች የተፈጠሩባቸው ሀገራት እንዳሉ ሁሉ ምሳሌ መኾን የሚችሉ ምርጫዎችን አድርገው ሀገራቸውን በበጎ ያስጠሩ እና ብዙ ኢንቨስትመንቶችን የሳቡ ሀገራት እንዳሉም አንስተዋል።
ኢትዮጵያም አነሰም በዛም ችግሮች እንኳን ቢኖሩባት በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚገጥም ግን ደግሞ በጊዜ ሂደት እየተስተካከለ የሚሄድ በመኾኑ ለምርጫ ትኩረት መስጠት እንደሚገባት አስረድተዋል።
ምርጫ ካለማካሄድ እና በምርጫው ንቁ ተሳታፊ ካለመኾን ምርጫን ማካሄድ እና ከፍ ያለ ተሳትፎ ማድረግ ችግሮችን እንደሚፈታ በማሰብ በምርጫው ወሳኝ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
#ምርጫ #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
