
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ምህዳሩ መስፋቱን ተከትሎ ፓርቲዎች ከመካሰስ እና ከመሳደድ በመውጣት አብሮ የመሥራት ባሕልን ማዳበር መቻሉን አንስተዋል።
ችግሮች ሲያጋጥሙ በጋራ ምክር ቤት መድረክ እየተወያየን ችግሮችን እየፈታን ዘልቀናል ብለዋል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚደረገው ዝግጅትም የእጩዎች እና የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ በሌሎችም ተግባራት ላይ በመናበብ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የጋራ ምክር ቤቱንም ከግጭት መለስ በሀሳብ የመሟገት ባሕል ለማሳደግ ተጠቅመንበታል ነው ያሉት። ሕዝባችንም የሚበጀውን ለመምረጥ መወሰን የሚያስችል ዕድል አግኝቶበታል፤ በሂደቱ ጥሩ የዴሞክራሲ ልምምድ ተገኝቶበታል ብለዋል።
ሕዝቡም በክልላችን ባለበት የግጭት ሁኔታ ውስጥ ኾኖ የመራጮችን ካርድ በማውጣት የሰላም ጥማቱን እና የዴሞክራሲ መራጭነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል። ከግጭት ይልቅ በሠለጠነ መንገድ መሪውን የመምረጥ ብርቱ ፍላጎቱን ማሳየቱንም ገልጸዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ሕዝቡ በምዝገባ ያሳየውን ሰፊ ፍላጎት በድምፅ መስጫ ቀንም በመውጣት ድምጹን እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከምርጫም በላይ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር እንዲያሸንፉ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
እስካሁን በነበረው ሂደት ንቁ ተሳታፊ ለነበረው መላው ሕዝብ፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሚዲያ ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
የምርጫ አሥፈጻሚ አካላት፣ ሚዲያዎች እና የፀጥታ ተቋማት ቀሪ ሀገራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም በአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
