በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለማረም የመምህራን ሚና ቁልፍ ነው።

8
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ከመምህራን ጋር ውይይት አካሂዷል።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) መምህራን የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት በማጠናከር ሀገር ወደ ብልጽግና በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲኾኑ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም በምርጫ ሂደት እና ከዚያም በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ የሰላም መደፍረሶችን ለመከላከል የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ የሚታዩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ውጥረቶችን ለማረም የመምህራን ሚና ቁልፍ እንደኾነም ጠቁመዋል። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል እና ተማሪዎች ያለምንም ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌታዊ ሀገርነት ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የምሁራን ተሳትፎ እና ዕውቀት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ምሁራን ግንዛቤ በመፍጠር፣ ሂደቶችን በመምራት እና ተጽዕኖዎችን በማስገንዘብ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በተለይም በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፎች የሠለጠነ የሰው ኅይል ማፍራት ለሀገር ብልጽግና ቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ባለፉት ዓመታት የነበሩ የሰሜኑ ጦርነት እና መሰል ግጭቶች ለሀገር ግንባታ እንቅፋት መኾናቸውንም አስታውሰዋል። ከዚህ በኋላ ሥልጣን በጠመንጃ ሳይኾን በሕዝብ ድምጽ እና በምርጫ ካርድ ብቻ የሚገኝበትን የዴሞክራሲ ሥርዓት ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።
ባለፉት አምስት ዓመታት ተቀናቃኝ ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በማድረግ፣ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በመተግበር እና በማኅበራዊ ዘርፎች ሰፊ ሥራዎች በመከናወናቸው ተስፋ ሰጭ ለውጦች መመዝገባቸው ተመላክቷል።
በቀጣይም ፓርቲው የጀመራቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ፣ ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን እና የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በትውልድ ቅብብሎሽ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less
Previous articleአንጻራዊ ሰላም መኖሩ በላሊበላ ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ አድርጓል።
Next article“በምርጫው ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና ሀገር ማሸነፍ አለባቸው” አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ