
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓይኖች በስስት ይመለከቱታል፤ የሰው ልጅ የኪነ ጥበብ በረከት በሕያው ምስክርነት ተቀምጦበታል፤ ጎብኝዎች በረከትንና የመንፈስ እርካታን ይዘው ይመለሱበታል፤ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት።
የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ቅርሱን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን እግር አጥበው እና በፍቅር ተቀብለው በጎብኝዎች ላይ ድንቅ ትውስታን ፈጥረው ይልካሉ።
በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ ባጋጠመው ግጭት ምክንያት ላሊበላ ከተማ ጎብኝ ናፍቋት ቆይቷል። ነዋሪዎቹም በፍቅር የሚቀበሉት፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያሳልጥላቸውን ጎብኝ በራቸውን ከፍተው፤ እጃቸውን ዘርግተው ጠብቀዋል።
የመንግሥት የሰላም ጥሪ እና የታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበል ደግሞ የከተማዋን ነዋሪዎች እንደ ጥዋት ጀምበር ገጻቸውን አፍክቷል።
በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ መነቃቃትን በመፍጠሩ ዳግም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ አድርጓል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጀ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መነቃቃት እያሳየ መኾኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸው የአካባቢው ቱሪዝም እንዲነቃቃ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የቱሪዝም ፍስሰቱ መሻሻል እያሳየ ቢኾንም እንኳ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እና የአካባቢው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተሻለ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ሰላም እና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ በመኾናቸው ሰላምን ይበልጥ በማጽናት ማኅበረሰቡ ከቱሪዝም ልማት ይበልጥ ተጠቃሚ ሊኾን እንደሚገባም ገልጸዋል።
በከተማዋ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ እንደኾነም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
