“እኛም የሀገራችን ዕጣ ፈንታ የሚወስነውን አካል በካርዳችን እንመርጣለን” የቤት ሠራተኞች

5
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች እኩል የሚሳተፉበት እና የነፃነት መብታቸውን የሚጠቀሙበት እንዲኾን ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ ሂደትም የቤት ውስጥ ሠራተኞች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማረጋገጥ እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው።
ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቤት ውስጥ ሠራተኞች ፍቅር ደስታ እና ጀማወንዝ ይመኑ በምርጫው ለመሳተፍ ካርድ በእጃቸው ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አሠሪዎቻቸው አስፈላጊውን ፈቃድ እና ድጋፍ በማድረጋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ጠቅሰው “የቤት ሠራተኛ መኾን ለመምረጥ አያግደኝም፤ ድምፄ ዋጋ አለው” በሚል ስሜት የሚወክላቸውን ፓርቲ ለመምረጥ እየተጠባበቁ መኾኑን ተናግረዋል።
የቤትውስጥ ሠራተኞቹ “እኛም የሀገራችን ዕጣ ፈንታ የሚወስነውን አካል በካርዳችን እንመርጣለን” ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ባንቻየሁ ተፈራ በበኩላቸው ማኅበሩ የቤት ሠራተኞችን መብት ከማስከበር ባለፈ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
ከ40 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ይህ ማኅበር፤ ቀደምት የምርጫ ተሳትፎው ዝቅተኛ የነበረ ቢኾንም ዘንድሮ ግን በርካታ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ካርድ እንዲያወጡ መደረጉን አብራርተዋል።
የቤት ውስጥ ሠራተኞች እንደማንኛውም ዜጋ እኩል የመምረጥ መብት እንዳላቸው የገለጹት ወይዘሮ ባንቻየሁ አሠሪዎችም ይህንን መብት የማክበር እና የማመቻቸት ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በተጨማሪም ሠራተኞች ከመምረጥ ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊነት የድርሻቸውን እንዲወጡሞ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየወገናቸውን ችግሮች በቴክኖሎጂ ለማቃለል እየተጉ ያሉት ተማሪዎች።
Next articleይጠንቀቁ፦ያልተጣሩ የጤና መረጃዎች ዋጋ ያስከፍላሉ!