የወገናቸውን ችግሮች በቴክኖሎጂ ለማቃለል እየተጉ ያሉት ተማሪዎች።

5
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የትራፊክ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የታዳጊዎች የፈጠራ ሥራዎች ተስፋ እየኾኑ መጥተዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች የአካባቢያቸውን ችግር መሠረት ያደረጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያቀረቡ ይገኛሉ።
ተማሪ መባጺወን ካሳ እና ተማሪ መክሊት በቀለ በግብርና እና በትራንስፖርት ዘርፍ ያበረከቷቸው የፈጠራ ውጤቶች ለዚህ በቂ ማሳያ ናቸው።
👉የአርሶ አደሩን ድካም የሚቀንሰው የታዳጊዋ ፈጠራ በእሸት አካዳሚ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የኾነችው ተማሪ መባጺወን ካሳ፣ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ቴክኖሎጂ ወሳኝ መኾኑን ታምናለች።
ተማሪ መባጺወን በአካባቢዋ የአርሶ አደሮችን ድካም ስትመለከት መቆየቷ የፈጠራ ሥራዋን እንድትጀምር ምክንያት ኾኗታል። ተማሪዋ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች አነስተኛ የሰብል መሠብሠቢያ ማሽን ሠርታ አቅርባለች።
“ግብርናን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር ካልተቻለ ምርታማነትን ማሳደግ አይቻልም” የምትለው ተማሪ መባጺወን መሰል የፈጠራ ሥራዎች በስፋት ተመርተው ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ የመንግሥትን ድጋፍ ይጠይቃል ብላለች።
👉የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተሠራው የ “ሴንሰር” የፈጠራ ሥራ ሌላኛዋ የፈጠራ ባለቤት የባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ መክሊት በቀለ ናት። መክሊት በትራፊክ አደጋ የሚጠፋውን የሰው ሕይወት እና ንብረት ለመታደግ የሚያስችል “የመኪና ሴንሰር” ሠርታለች።
በተለይ በድካም ምክንያት እንቅልፍ ለሚያሸንፋቸው የረጅም ጉዞ አሽከርካሪዎች መፍትሄ የሚሰጠው ይህ ሴንሰር፤ አደጋ ከመከሰቱ በፊት ድምጽ በማሰማት ወይም መኪናውን ራሱ እንዲቆም በማድረግ አደጋን ይከላከላል።
ወደፊት “አስትሮነመር” የመኾን ትልቅ ህልም ያላት ተማሪ መክሊት ለሥራዋ መሳካት ሥልጠናና ግብዓት እንደሚያስፈልጋት ትናገራለች።
“በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለመጨመር እና በትራንስፖርት ዘርፉ የሰውን ሕይወት ለመታደግ የታዳጊዎቹ ሚና የላቀ ነው።
መባጺወን እና መክሊት የጀመሩት የፈጠራ ሥራ በስፋት ተመርቶ ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ከታከለበት የሀገራችንን ችግሮች በሀገር በቀል ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ የመፍታት ህልማችን እውን መኾኑ አይቀርም።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleሰላም ባለበት ድምጽ ይሰማል፣ ድምጽ በተሰማበት ደግሞ የሕዝብ ፍላጎት ይከበራል።
Next article“እኛም የሀገራችን ዕጣ ፈንታ የሚወስነውን አካል በካርዳችን እንመርጣለን” የቤት ሠራተኞች