
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ በምርጫ ካርዳቸው ለመሳል ሲዘጋጁ፣ የጸጥታ መዋቅሩ ደግሞ ይህ የዜግነት መብት ያለ ስጋት እንዲፈጸም የሰላም አጥር ኾኖ ቆሟል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃና የነጋዴ ባሕር ከተሞች ልዩ የለውጥ መንፈስ ይታይባቸዋል።
እንደ ወጣት አብርሃም ስንታየሁ ያሉ ቀደም ሲል በፖለቲካው ረገድ “እኔ ምን አገባኝ” በሚል ዝምታን መርጠው የነበሩ ዜጎች፣ ዛሬ ያንን ቁጭት በመስበር ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጭነት ካርዳቸውን በኩራት ይዘዋል።
ወጣት አብርሃም “ምርጫ የገዛ እጣ ፈንታዬን የምጨብጥበት መሣሪያ ነው” ሲል፣ ለውጥ በቃላት ብቻ ሳይኾን በድምጽ መስጫ ካርድ እንደሚመጣ ያለውን ዕምነት ይገልጻል።
በአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ የምትኖረው ወጣት ሃይማኖት አለልኝም በተመሳሳይ፣ ይህ ምርጫ የሴቶችን እኩልነት እና ተጠቃሚነት የምታረጋግጥበት መድረክ እንደኾነላት ትናገራለች።
እንደ አቶ ደረሰ ገለጻ ምርጫው በታማኝነት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን ልዩ “የምርጫ ግብረ ኀይል” ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ምርጫ ሰላምን እንደሚሻ የጠቀሱት ኀላፊው ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሹ የውስጥ እና የውጭ ኀይሎች ቢኖሩም፣ የጸጥታ መዋቅሩ ግን ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ መኾኑን ገልጸዋል።
“ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጀምሮ መደበኛ ፖሊስ፣ አድማ መከላከል እና ሚሊሻ እስከ ሱዳን አዋሳኝ ድንበር ድረስ ተሰማርተው አካባቢውን እየጠበቁ ይገኛሉ” ይላሉ አቶ ደረሰ።
እስካሁንም ድረስ በምርጫ ሂደቱ ላይ ያጋጠመ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አለመኖሩን የገለጹት ኀላፊው፣ መራጮች ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ያለምንም ስጋት ወጥተው እንዲመርጡ የሚያስችል የሰላም ዓውድ መፈጠሩንም አረጋግጠዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚታየው ይህ ዝግጅት አንድ ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል፤ ሰላም ባለበት ድምጽ ይሰማል፣ ድምጽ በተሰማበት ደግሞ የሕዝብ ፍላጎት ይከበራል። እንደ አብርሃም እና ሃይማኖት ያሉ ወጣቶች የጣሉት የዴሞክራሲ ተስፋ፣ በጸጥታ ኀይሉ የሰላም ጥበቃ ታጅቦ ለታላቁ የምርጫ ቀን ቀጠሮ ይዟል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
