
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ ከመኾን ጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
ምርጫው ሰላማዊና ታማኒ እንዲሆን መደረጉ ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ መኾኑን የተናገረው ወጣት ሹምበላይ ያየህ ነው።
ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅም ከወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ባለፈ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሴቶች ሚና ከፍተኛ መኾን እንዳለበትም ተናግሯል።
ዜጎችም የፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ እና ፖሊሲዎች በማነጻጸር ለሀገር ይበጃል የሚሉትን እንዲመርጡ መክሯል።
መራጮች የድምፅ መስጫ ካርድ ከመውሰድ ባለፈ በዕለቱ ተገኝተው ድምፅ የመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸውና እሱም ለዚህ መዘጋጀቱን ገልጿል።
ወጣት ወይንሸት አጥናፍ በበኩሏ ምርጫው ለወጣቶች ሀገር ተረካቢነት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ለምርጫ ካርዱ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብላለች።
ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅ ማኅበረሰቡን በማንቃት ሥራ ላይ መኾኗንም ተናግራለች።
ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጹን ለመሥጠት መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ሀብታሙ ዘለቀ ነው። የምርጫ ካርድ መውሰዱንና በቀጣይም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ ኾኖ እንዲቀጥል የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ ነኝም ብሏል።
በምርጫ ቀን በሰዓቱ በመገኘት ነገ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብሎ የሚያምነውን ለከተማዋም ኾነ ለሀገሪቱ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ በመጠባበቅ ላይ መኾኑን አስረድቷል። የምርጫ ካርድ ያወጡ መራጮችም ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው መክሯል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
