
አዲስ አበባ: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባን ዘመናዊ የከተሜነት ጉዞ የሚዳስስ ሲምፖዚየም ተካሂዷል። ሲምፖዚየሙ ኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጋር በጋራ “አዲሲቷ አዲስ” በሚል መሪ መልዕክት የተዘጋጀ ነው።
በሲምፖዚየሙ ላይ ከተመሠረተች 140 ዓመታት እንደኾናት ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማ ማደስ እና ማስዋብ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቷም ተገልጿል።
ይህን ፈጣን የከተማዋ የዕድገት ጉዞ በሌሎችም ዘርፎች ለመተግበር የሚያስችል ተሞክሮ ለመውሰድ እና ከፈጣን ዕድገቷ እኩል የሚራመድ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ሲምፖዚየሙ ወሳኝ ነው ተብሏል።
በሲምፖዚየሙ ከተሞች እና የአዲስ አበባ ዘመናዊ ጉዞ ታሪካዊ ዳራ እና ልምዶች፣ የከተማ ትራንስፎርሜሽን እሳቤዎች ትግበራ እና እንድምታዎች በአዲስ አበባ
የሚሉ ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከተሞች ከኢኮኖሚ አንፃር ቢፈጠሩም አዲስ አበባ ግን አጠቃላይ ዕድገቷ በፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተንተራሰ መኾኑ በጥናታዊ ጹሑፉ ላይ ቀርቧል።
የከተማ ዕድገት መሠረታዊያን የሚባሉትን ሰው ተኮር፣ ለኑሮ ምቹ፣ ተወዳሪ፣ ዕኩል ተጠቃሚነት፣ ፍትሐዊ ከተማነት የሚባሉ መለኪያዎችን እንድታሟላ ትልቅ ሥራ መሠራቱም ተመላክቷል። ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በጥራት ደረጃውን ጠብቆ በመገንባት የተገኘው ልምድም የሚበረታታ ነው ተብሏል።
በጥናታዊ ጹሑፉ የከተማዋ ጉዞ ከነገሥታቱ እስካሁን ባለው የመንግሥታት የለውጥ ሂደት ምን እንደሚመስልም የሚያስቃኙ ፎቶግራፎች ቀርበዋል። በመርሐግብሩ ላይ የዘርፉ ምሁራን የሚዲያ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
አሚኮ #ዜና #የከተማልማት_አዲስአበባ #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
