
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ለበርካታ ዓመታት በክልል ደረጃ ባለው የመንግሥት እርከን በጽሕፈት ቤት ደረጃ ነበር ተዋቅሮ የቆየው። በቅርቡ አደረጃጀቱ ወደ ኮሚሽን ከፍ ብሏል።
ተቋሙ በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ የጀመረበትን የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ከተቋማዊ ሪፎርሙ ጋር በማስተሳሰር በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።
ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ወደ ኮሚሽን ከፍ ማለቱ ተቋሙ ራሱን ችሎ ለመፈጸም እና ለጠንካራ የሚሊሻ ኀይል ግንባታ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የሚሊሻ ኀይሉ በአቅም እንዲገነባ፣ በሥልጠና እንዲዳብር፣ በሰው ኀይል እና በግብዓት የተሟላ እንዲኾን ያስችለዋል ነው ያሉት። ይህም ለሚሊሻ ኀይሉ ክብር የሚሰጥ፣ ሞራል የሚገነባ፣ ለበለጠ ግዳጅ የሚያነሳሳ፣ ተስፋ የሚሰጥ ተቋማዊ ሪፎርም መኾኑን አብራርተዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግም የክልሉን ሰላም በአስተማማኝ ደረጃ በራስ አቅም ለመጠበቅ የሚያስችል የሚሊሻ ኀይል እየተገነባ መኾኑን አስታውቀዋል። ሚሊሻ ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች አደረጃጀት የሚለየው በየትኛውም አካባቢ ከሕዝቡ ጋር አብሮ የሚኖር በመኾኑ ነው ብለዋል።
ይህንን ኀይል በአግባቡ ማደራጀት እና ዕውቅና መስጠት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መኾኑንም አስረድተዋል። የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ሲከበርም ይህንን መሠረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ መከበር ለሚሊሻ ኀይሉ ዕውቅና በመስጠት ተቋሙን፣ ሀገሩን እና ሕዝቡን የበለጠ አክብሮ በተነሳሽነት እና በባለቤትነት ስሜት እንዲሠራ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በቀጣይም የክልሉ የሚሊሻ ኀይል ባለፉት የቀውስ ጊዜያት ላበረከተው አስተዋጽኦ፣ ለከፈለው መስዋትነት እና ለፈጸመው ጀብዱ በሚመጥን መልኩ በክልል ደረጃ እንደሚከበር ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #አማራ_ክልል #ሚሊሻ #ሰላም #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
