
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች የሀገሪቱ የሥልጣን ምንጭ መኾናቸውን በተግባር የሚያሳዩበት መንገድ ነው። አንድ ዜጋ በሰጠው ድምጽ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም ይኖረዋል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኘነት ትምህርት ክፍል መምህር አበራ ታደሰ ምርጫ ዜጎች በድምፃቸው ይመራኛል የሚሉትን ፓርቲ የሚመርጡበት ሥርዓት መኾኑን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት አይነተኛ መንገድ እንደኾነ ነው ያስረዱት።
የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በጸጥታ ችግር ውስጥ የነበረ ቢኾንም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መሳተፉ በርካታ እድሎችን ይዞ ሊመጣ የሚችል መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት የሚያስችል እንደኾነም ገልጸዋል።
በምርጫ የሚመጣ መንግሥት ተቀባይነት ያለው ጠንካራ ሕግ እና ሥርዓትን የሚከተል አንደሚኾን ይታመናል ነው ያሉት። ምርጫው ለዘላቂ ሰላም አይነተኛ መሣሪያ ነውም ብለዋል።
በክልሉ የሚደረገውን ምርጫ ሕዝቡ በንቃት ሲሳተፍ የተሻለ ሰላም ፈላጊ መኾኑን ማሳያ ነውም ብለዋል። ይህም የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድን የበለጠ እንደሚያጎለብተው አስረድተዋል። ድምጽ በመስጠትም የሰላም ዘብ መኾኑን የሚያሳይበት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ምርጫ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች በሠለጠነ መንገድ የሚስተናገዱበት መድረክ በመኾኑ ማኅበረሰቡ የመቻቻል ባሕልን እንዲያዳብር ይረዳል ነው ያሉት። ዛሬ በምርጫ የምናሳየው የሰላማዊ ውድድር ባሕል ለሚቀጥለው ትውልድ እንደ ታላቅ ቅርስም ይተላለፋል ብለዋል።
ይህም ትውልዱ ችግሮችን በውይይት እንጂ በጦርነት የመፍታት አባዜን እንዲተው እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ምርጫ በቀላል የሚታይ ነገር አይደለም ያሉት መምህሩ በምርጫ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ይመረጣል፤ የዴሞክራሲ ባሕልም ያድጋል ነው ያሉት።
ስለዚህ ምርጫ፦
🗳️ የሕዝብ ቅቡልነት እና የሥልጣን ሽግግር
👤 የዜጎች የሥልጣን ምንጭነት
🤝 የዳበረ ዴሞክራሲ
🇪🇹 ሰላማዊ እና ጽናት ያላት ሀገር ይገነባል ብለዋል።
በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንብታ ውስጥ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ እና ታማኝነት ያለው ምርጫ ወሳኝ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ተመራጩ ባገኘው ድምጽ ሀገሩን ይመራል፣ ማኅበረሰቡ በሰላም አብሮ ይኖራል፣ ትውልም የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ያላት ሀገርን ይረከባል፤ ስለዚህ ምርጫ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሣሪያ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
#አሚኮ #ምርጫ2018 #አማራክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
