600 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

6

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት 10 ወራት 600 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡን አስታውቋል።

የተሠበሠበው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ257 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ (ዶ.ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሠበሠበው ገቢ ለሀገሪቱ ትልልቅ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ እና ቀጥታ ወደ መንግሥት ካዝና የሚገባ ነው ብለዋል።

በድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት የሕግ ተገዥነታቸው ከተጓደለ አስመጭዎች፣ ላኪዎች እና አምራቾች 20 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።
ዝቅተኛ የሕግ ተገዥነት ካለባቸው የኮሚሽኑ ደንበኞች ደግሞ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።

የቀረጥ ነጻ ማበረታቻን ያለአግባብ ከተገለገሉ አካላት ሀገር ልታጣ የነበረውን 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለም በመግለጫቸው አንስተዋል።

በተሠራ የኮንትሮባንድ መከላከል እና የቁጥጥር ሥራ ከገቢ ኮንትሮባንድ 21 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፤ ከወጭ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በጥቅሉ 23 ቢሊዮን ብር በቁጥጥር ስር በማዋል ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል።

1 ሺህ 295 የሚኾኑ በኮንትሮባንድ የተሠማሩ ግለሰቦች ተይዘው ለሕግ መቅረባቸውንም ገልጸዋል።

ለበጀት ዓመቱ የ10 ወራት አፈጻጸሙ ስኬተ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መደረግ እና ተቋማት በየጊዜው የሚሠሯቸው የሪፎርም ተግባራት ሚናቸው ከፍተኛ እንደነበርም አንስተዋል።

የኮንትሮባንድ ችግር አለመቀረፍ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት መኖር ለኮሚሽኑ ሥራ ችግሮች መኾናቸውን አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየወጣቶች ድምጽ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ዋጋ አለው።
Next article“ኢትዮጵያ የላቀ ሚና መጫወቷን ትቀጥላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)