የወጣቶች ድምጽ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ዋጋ አለው።

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “በወጣቶች ሀሳብ ኢትዮጵያን ወደተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ከወጣቶች ጋር የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል።

የባሕርዳር ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ወጣቶች የሀገር ተረካቢ እና የኅብረተሰቡ ትልቁ የሰው ኀይል መኾናቸውን ተናግረዋል። በልማት እና በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ወጣቶች ያለባቸውን ከፍተኛ ኀላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል። ቀደም ብለው የምርጫ ካርድ በማውጣት ላሳዩት ዝግጁነትም ምሥጋና አቅርበዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና ሀገሪቱ ከድህነት እንድትወጣ ወጣቶች የብልጽግናን መንገድ እንዲደግፉም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶችን እንደ ተራ ተከታይ ሳይኾን እንደ ሀገር ግንባታ ዋና ተዋናይ እና መሪ አድርጎ እንደሚመለከት ገልጸዋል።

የወጣቶች ድምጽ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ዋጋ እንዳለው ጠቁመዋል። ወጣቶች ካለፈው የታሪክ ቁስል በመውጣት ለዘላቂ ሰላም እና ለተሻለ መጻዒ ተስፋ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ከፍተኛ ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

የባሕር ዳር ወጣቶች ቀደም ሲል በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ወቅት ከተማቸውን ለመጠበቅ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አስታውሰዋል።
አሁንም ሰላምን ለማጽናት እና የነገዋን ኢትዮጵያ በጋራ ለመገንባት በከፍተኛ ትጋት እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

#አሚኮ #ምርጫ2018 #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleሀሰተኛ መረጃን መከላከል ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ወሳኝ ነው።
Next article600 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።