ሀሰተኛ መረጃን መከላከል ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ወሳኝ ነው።

6

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምርጫ ወቅት የሚሰራጩ የሀሰተኛ መረጃዎች በምርጫ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። መራጮችን በማደናገር የሚፈልጉትን አካል በነፃነት እንዳይመርጡ እና የተሳሳተ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ያደርጋል፡፡

የተሳሳቱ መረጃዎች የምርጫውን ውጤት ተቀባይነት በማሳጣት ለድህረ ምርጫ ሁከት ምክንያት ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ በዕጩዎች ላይ የሚሰራጩ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችም ፍትሐዊ የውድድር መንፈስን ይገድላሉ፡፡

በአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የዕውነታ ማጣራት አሠልጣኝ አብነት ቢኾነኝ እንደሚሉት በምርጫ ወቅት ሀሰተኛ መረጃዎች መረጃን በማሳሳት፣ በማዛባት ወይም በመበከል ሊሰራጩ ይችላሉ።

በዚህም የምርጫ አሥፈጻሚ አካላት፣ የዴሞክራሲ እና የሚዲያ ተቋማት ያላቸውን ተአማኒነት እንዲሸረሸር በማድረግ በምርጫ ሂደት ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።

በምርጫ ወቅት የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል:-

✅ በዋናነት የሚዲያ አጠቃቀም እና የመረጃ ግንዛቤን ማሳደግ፣

✅ ዜጎች የሚደርሷቸውን መረጃዎች ከመቀበላቸው እና ከማጋራታቸው በፊት የመረጃውን ትክክለኛነት ከምንጩ ማጣራት፣

✅ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን ከመንግሥት እና ከታወቁ የሚዲያ ተቋማት ጋር በማነፃፀር ማረጋገጥ፣

✅ የመረጃ ማጣሪያ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ መንገዶችን መጠቀም፣

✅ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሠሩ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ለመለየት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣

✅ ኀላፊነት ያለባቸው የሚዲያ ተቋማት ለዜጎች ተደጋጋሚ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ፣

✅ማኅበራዊ ሚዲያን የማይጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተሳሳተ አሉባልታ እንዳይጋለጡ የምርጫ መረጃዎችን በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ቀጣይነት ያለው መረጃ መስጠት፣

✅እያንዳንዱ ዜጋ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና የሚዲያ ተቋማት በምርጫ ወቅት የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች የምርጫ ሂደቱን ሊያደናቅፉ እንደሚችሉ ተገንዝበው መረጃን በማጣራት የበኩላቸውን ኀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

#አሚኮ #ምርጫ2018 #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለስምንት ምሁራኑ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።
Next articleየወጣቶች ድምጽ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ዋጋ አለው።