
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ አሥተዳደርን የሚለማመዱበት እና ሕዝባዊ መንግሥት የሚመሠረትበት ሥርዓት ነው።
ይህ ሂደት ፍሬያማ የሚኾነው ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጥላቻ እና ከሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ይልቅ የሀገርን ልማት እና የሕዝብን አንድነትን ማዕከል ያደረገ የርዕዮተ ዓለም ክርክር ሲያደርጉ ብቻ እንደኾነ ይነሳል።
በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አሕመድ ኡስማን ሀገራት በመተማመን ላይ የተመሠረተ ምርጫን ያስኬዱ ዘንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕግን እና አዋጅን መሠረት አድርገው መንቀሳቀስ ግድ ይላቸዋል ብለዋል።
በሕዝብ ዘንድ ተመራጭ ኾኖ ለመገኘት ሀገርን እና ወገንን ያስቀደመ ጤናማ እንቅስቃሴ መዳበር አለበት ነው ያሉት። ከገዥው ፓርቲ ጋርም ኾነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለ ግንኙነት እና ፉክክር በሀሳብ በልጦ የመገኘት መርህን ያነገበ መኾን እንዳለበት ገልጸዋል።
ለጋራ ሀገር ሲባል ፓርቲዎች ሕጋዊ ካልኾኑ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸውም መክረዋል። የመመረጥ ዕድላቸውን የማስፊያ መንገዳቸው የተሻለ ሀሳብ ይዞ መቅረብ እና ማስገንዘብ ሊኾን እንደሚገባም አንስተዋል።
ተፎካክሮ መሸነፍ እና ማሸነፍ ያለ ነው የሚሉት መምህሩ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን የሀገርን ሰላም ማስቀደም መቻል ሳይንሳዊ ተግባር ነው ብለዋል።
ሀገር ችግር ላይ ከወደቀች መመለሻዋ ሩቅ ነው ያሉት መምህሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገራቸው መጻኢ ዕጣ ፈንታ ሊያሳስባቸው ይገባል ነው ያሉት።
የየትኛውም ሀገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በአንድ ጀንበር የመጣ አይደለም፤ መልካም ልምምድን ማምጣት ለሀገር ዕድገት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል። በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይም ፓርቲዎች ሕግን እና ሀገራቸውን አስቀድመው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም በአጽንኦት አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
#ምርጫ #ኢትዮጵያ#
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
