
ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በትራፊክ መጨናነቅ ሰዓታትን ማሳለፍ፣ በመንገድ አደጋ ስጋት መኖር እና በወረቀት የታጀበው የትራፊክ አሥተዳደር በኢትዮጵያ ከተሞች የሁልጊዜ ፈተናዎች ናቸው።
በባሕር ዳር ከተማ የብጹዕ ገብረ ሚካኤል ካቶሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የኾነው አብርሃም አበበ ለዚህ ችግር ዘመናዊ እና የተቀናጀ መፍትሔ ይዞ መጥቷል።
“ስማርት ትራፊክ ማኔጅመንት” የተሰኘው ይህ ዲጂታል ፕላትፎርም፣ ከመደበኛ አፕሊኬሽን ባለፈ የትራፊክ አዛዦችን፣ ኦፊሰሮችን፣ ታክሲዎችን እና አሽከርካሪዎችን በአንድ መስመር ውስጥ የሚያገናኝ ዘመናዊ ሲስተም ነው።
👉 የአብርሃም ፈጠራ ምን ለውጥ ያመጣ ይኾን?
ከተዝረከረከ የወረቀት አሠራር ወደ ዲጂታል፦
የትራፊክ ቅጣት፣ የአደጋ ሪፖርት እና የታክሲ ፌርማታ አሥተዳደር ሙሉ በሙሉ በዲጂታል በመኾኑ የወረቀት ሥራን ያስቀራል፤ ግልጽነትን በመፍጠር ሙስናን ይከላከላል።
👉 ብልህ የትራፊክ ፍሰት
ስማርት ካሜራዎችን በመጠቀም የመንገድ መጨናነቅን ይለያል፤ ፍሰቱን ያስተካክላል፤ አደጋዎች ሲከሰቱ አፋጣኝ ጥቆማ ይሰጣል። ካሜራ በሌለባቸው ቦታዎችም በኦፊሰሮች እና በተጠቃሚዎች መረጃ ሥራውን በብቃት ያከናውናል።
ታክሲዎች እና የግል ተሽከርካሪዎች መጨናነቅ የሌለበትን እና ፈጣኑን መንገድ እንዲመርጡ (Route Planner) በማገዝ ነዳጅ እና ጊዜን ይቆጥባል።
ይህ ፕሮጀክት የአንድ ታዳጊ የፈጠራ ውጤት ብቻ ሳይኾን፣ “ዲጂታል ኢትዮጵያን” (Digital Ethiopia) እውን ለማድረግ እና የመንገድ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ትልቅ መፍትሔ ነው። በፈጠራ ሥራው በአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ተሸላሚ የኾነው አብርሃም በትምህርት ገበታ ላይ ኾኖ የማኅበረሰቡን ትልቅ ሕመም የሚፈውስ ቴክኖሎጂ በማቅረቡ ለተከታዮቹ አርዓያ ኾኗል።
በአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ የሥልጠና ሙያተኛው ሃብታሙ ላቀ ለተማሪዎች በመካኒካል እና ሶፍት ዌር ዘርፎች በቴክኖሎጅ ፈጠራ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል።
የሥልጠናው ዓላማ ተማሪዎች ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ የፈጠራ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና ለወደፊቱም በሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዘርፉ የፈጠራ ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻል ነው ብለዋል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
