
ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በገበያ ላይ የበርበሬ ዋጋ መናር ሸማቹን ክፉኛ እያማረረ ነው። አምራች አርሶ አደሮች ደግሞ በበሽታ ምክንያት ምርቱ በመቀነሱ የልፋታቸውን ዋጋ እያጡ እንደኾነ ሲገልጹ ይስተዋላል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ አርሶ አደር ደመላሽ አያና ስር አበስብስ እና ቃሪያ አውላቂ ሲሉ የጠሯቸው በሽታዎች ተጠቃሚነታቸውን እየፈተኑት መኾኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ከፍተኛ ወጭ አውጥተው እና ደክመው ያመረቱት ሰብል ክረምት በወጣ ማግስት በበሽታ ሲረግፍ ማየታቸው መሬታቸው ጾም እንዲያድር እና ለከፍተኛ ኪሳራ እንዲዳረጉ ያደረገ ነው ብለዋል።
የሚመለከተው አካል የችግሩን ምንጭ መርምሮ አስቸኳይ ሙያዊ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
የወራሚት አትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል አርሶ አደሮች የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በሄክታር እስከ 36 ኩንታል ምርት የሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎችን ለማስተዋወቅ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የወራሚት አትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል ዳይሬክተር እና የአትክልት እና ፍራፍሬ ተመራማሪ ምንውዬለት ጀምበሬ አዲሱ ዝርያ ከነባሮቹ የበርበሬ አይነቶች ከ16 ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ነው ብለዋል። የተሻሻሉ ዝርያዎችም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለአርሶ አደርች ይሠራጫሉ ነው ያሉት።
እንደ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ ወንበርማ፣ አየሁ ጓጉሳ እና ቻግኒ ያሉ አካባቢዎች ለምርቱ መቀነስ ዋናው ምክንያት ባክቴሪያል ዊልት የተሰኘው በሽታ እንደኾነ ጠቁመዋል። በሽታው ከ50 በመቶ የምርት መቀነስ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ የሚያሳጣ እንደኾነም ገልጸዋል።
ከአየር ንብረት መለዋወጥ፤ ከዝርያ መዳከም እና አርሶ አደሮች ምንጩ ያልታወቀ ዘር ከመጠቀማቸው ጋር የተያያዘውን ለችግሩ መንስኤነት አንስተዋል።
በሽታውን ሙሉ በሙሉ የሚከላከል ዝርያ እስካሁን እንዳልተገኘም ጠቁመዋል። ምክንያቱ ደግሞ በክልሉ የበርበሬ ዘር አምራች ተቋም የለም ነው ያሉት። አሁናዊ መፍትሔ ግን አርሶ አደሮች ሳይንሳዊ የአመራረት ዘዴዎችን በመከተል የምርት ብክነቱን እስከ 90 በመቶ መቀነስ ይቻላል ብለዋል።
አርሶ አደሮች ዘርን ከመትከላቸው በፊት:-
👉 በጸረ ፈንገስ (አፕሮኖ ስታር) ኬሚካል ማከም፦
👉 ችግኞችን ወደ ማሳ ከመውሰዳቸው በፊት ሥራቸውን በሪዶሚል መዘፍዘፍ፦
👉 ችግኝን በመደብ መትከል
👉 በሽታው በአፈር ውስጥ እንዳይቆይ ለማድረግ የሰብል ማፈራረቅ ስልትን መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ማፈራረቁ ግን ከበርበሬ ዘር ውጭ ከኾኑት እንደ ድንች እና ቲማቲም መኾን እንዳለበት ጠቁመዋል። በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት አጋዥ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በቡሬ እና አካባቢው መረቆ ፋና የተሰኘው ዝርያ የተሻለ መኾኑንም ጠቁመዋል። ከ54 በላይ አርሶ አደሮች በዝርያ ማባዛት እና ማላመድ ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙም ተመራማሪው አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
