ለምርጫ የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ መኾናቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

3

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ ኾኖ ለመውጣት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ መኾናቸውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ(ኢዜማ) አስታውቀዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ጸጋዬ ፓርቲያቸው ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ከዓመት በፊት ጀምሮ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም የፖሊሲ ሰነዶችን የማዘጋጀት፤ የምርጫ ዘመቻ መርሐ ግብሮችን የማደራጀት እና ዕጩዎችን የመለየት ተግባራት በስፋት ተከናውነዋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፓርቲው በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች ዕጩዎቹን አስመዝግቦ ወደ ንቅናቄ መግባቱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ስጋት በነጻነት ለመንቀሳቀስ ፈተና መኾኑን ያነሱት ምክትል ሊቀመንበሩ ፓርቲው አማራጭ የኾኑ የማኅበራዊ ሚዲያ እና የዲጂታል መድረኮችን ለመጠቀም እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የምርጫ ምልክቱም ሰዓት መኾኑን ጠቁመዋል።

ዴሞክራሲ በአንድ ጀምበር የሚገነባ ባለመኾኑ አብን ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ በሂደቱ ውስጥ እንደሚያልፍ እና ሕዝቡ ነባራዊ ሁኔታዎችን መዝኖ የተሻለ መፍትሔ የሚሰጠውን አካል እንዲመርጥ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የሰሜን ጎጃም እና የባሕር ዳር አካባቢ የምርጫ አሥተባባሪ ይበልጣል አድማሴ ፓርቲያቸው በምርጫው አሸናፊ ኾኖ ለመውጣት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረገ መኾኑን አስታውቀዋል።

ኢዜማ ሁሉም ዜጋ በሰላማዊ መንገድ እና በዕኩልነት የሚተዳደርበትን ሥርዓት ለመገንባት አልሞ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

ምርጫ ኢትዮጵያን ከጽንፍ እና ከጠመንጃ ፖለቲካ አውጥቶ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መኾኑንም አንስተዋል። ሕዝቡ የፓርቲዎችን የፖሊሲ ሰነዶች በማንበብ እና በማገናዘብ የሚፈልገውን አካል እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል። የኢዜማ የምርጫ ምልክታቸው ሚዛን መኾኑን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየ11ኛ ክፍል ተማሪው የስማርት ሲስተም ፈጠራ
Next articleምርጫው ሰላማዊ እና ስኬታማ እንዲኾን እየተሠራ ነው።