
ባሕርዳ፡ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሰባተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫን በማስመልከት ከጠቅላላ መንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።
ፓርቲው በአሥተዳደር እና ፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ዘርፍ፣ በከተማ እና መሠረተ ልማት ክላስተር ነው ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር የተወያየው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን መጭው ጊዜ ከሀገር ባሻገር የባሕር ዳር ከተማ እና ነዋሪዎቿ ከፍታ የሚበሰርበት እንዲኾን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታሪክ ሠሪ እጩዎችን መምረጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞች ድርሻ ጉልህ እንደኾነ ነው የጠቀሱት። በተለይም ደግሞ የምርጫን ጠቀሜታ እና የሀገረመንግሥትን ግንባታ ተረድተው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ ተሳትፎ በማድረግ ዓርያ ሊኾኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች ደግሞ የምርጫ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የቀጣይ አምስት ዓመት ማኒፌስቶ በተለያዩ አጋጣሚዎች ማድመጣቸውንም ገልጸዋል።
ይህንን ማኒፌስቶ ለመገንዘብ መንግሥት ሠራተኛው ከሌላው ማኅበረሰብ የተሻለ ዕድል ስላለው ቀጣይ በተግባር ሀገርን የሚያሻግር እና ሕዝብን የሚጠቅም ፓርቲ ለመምረጥ እንደ መንግሥት ሠራተኛ ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ሰላማዊ ምርጫ እንዲኖርም በዓርያነት ጥረት እናደርጋለን ነው ያሉት። የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም እንደሚያሳየው በምርጫ ምሁራኑ ግንባር ቀደም እንደኾኑ ገልጸዋል።
ዛሬ ብልጽግና ፓርቲ ያደረገው የመንግሥት ሠራተኞች መድረክም ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር እንደኾነም ገልጸዋል። በቀጣይም ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ ዓይነት የመንግሥት ሠራተኞች የውይይት መድረክ ይኖራቸዋል ብለው እንደሚጠብቁ ነው ያነሱት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
#7ኛው_ምርጫ #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
