“ልጆች ላይ መሥራት በነገ ሀገር ላይ መሥራት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

6

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤን አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የቀዳማይ ልጅነት ልማት አበባ እና አዝመራው፣ ከዛሬ ተሻግሮ በትውልዶች የሚሰበሰብ የሀገር ግንባታ ነው ብለዋል።

ዛሬ ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤን ማስጀመራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለልማት በምታደርገው ቆራጥ ጥረት ውስጥ የሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዋና ጉዳዮች አንዱ ነው ብለዋል።

መንግሥት መጪው ትውልድ ጤናማ፣ ብቁ እና ውጤታማ እንዲኾን የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ማዕከል በማድረግ ሁሉን አቀፍ ሥራን እየተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። የልጆች ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት፣ የምገባ ሥርዓት፣ የሕጻናት መጫወቻ ሥፍራዎች ግንባታ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች አምጥቷል ነው ያሉት።

ሀገር አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት እና ትምህርት ፖሊሲ የዘላቂ ብልጽግና መንገዳችን ከኾነው የመደመር እሳቤ ጋር በተናበበ መልኩ እየተተገበረ በስኬት ቀጥሏል ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የነጻና አስገዳጅ ትምህርት ተደራሽ እንዲኾን እያደረግን ነው።

ልጆች ላይ መሥራት በነገ ሀገር ላይ መሥራት በመኾኑ ይሄንን ትውልድ አስቀጥል ወሳኝ ተግባር ተባብረን፣ በጊዜ የለንም መንፈስና በትጋት እንድንሠራ በድጋሜ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ምርጫ የዴሞክራሲ መሠረት ነው።
Next articleብልጽግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት እየሠራ ነው።