
ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማከናወን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በአማራ ክልልም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር ) ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።
በክልል ደረጃ ዐቢይ ኮሚቴ ተደራጅቶ የማስፈጸሚያ ዕቅድ በማውጣት በየደረጃው ላሉት የጸጥታ መሪዎች ኦሬንቴሽን ተሰጥቷል። ይህንን መሠረት ተደርጎም አስፈላጊ ስምሪቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በዚህም በምርጫ ቦርድ በተፈቀዱት የምርጫ ጣብያዎች እና የምርጫ ክልሎች የምዝገባ ሂደቱ በስኬት መከናወኑን አስታውሰዋል። አሁን ላይ በምርጫ ወቅት ለሚኖሩ የጸጥታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
የምርጫውን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል የሁኔታ ትንተና ተሠርቶ ወደ ስምሪት መገባቱንም አመላክተዋል። ለዚህም የምርጫ ጣቢያዎችን በሦሥት የጸጥታ ደረጃዎች ከፍሎ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የጸጥታ ተቋሙ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን የምርጫ ቁሳቁሶችን፣ የአስፈጻሚዎችን እና የእጩዎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነቱን ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ምርጫው በሚካሄድበት ዕለትም ሕዝቡ በነጻነት ወጥቶ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ተቋሙ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
መንግሥት ማንኛውንም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመከላከል እና ሕግን ለማስከበር ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል። ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ እና የምርጫውን ሂደት ለማወክ የሚሞክሩ አካላትን መንግሥት እንደማይታገስም አስገንዝበዋል።
ሕዝቡም የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚወስንለትን እና የሚፈልገውን ፓርቲ ያለ ምንም ስጋት በነጻነት እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
