ሚሊሻ በአንድ እጁ ልማትን በመከወን፣ በሌላ እጁ ሰላምን የሚያረጋግጥ ኀይል መኾኑን አሳይቷል።

2

 

ከሚሴ: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር የሚሊሻ 30ኛ ዓመትን በማስመልከት የምሥጋና እና የዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።

የከሚሴ ከተማ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብዱረህማን አህመድ፣ የከተማው ሰላም አስከባሪ እና ሚሊሻ ሰላምን ለማስጠበቅ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ ነው ብለዋል። የከሚሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሸሪፍ ቃሲም በበኩላቸው የከተማው ሚሊሻ የከተማውን ሰላም በማጽናት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጽ፤ በቀጣይም የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅ አበክሮ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሱፍ አብዱ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሚሊሻ በሕልውና ዘመቻ ወቅት ትልቅ ገድል የፈጸመ መኾኑን ገልጸዋል። ሚሊሻ ከራስ አልፎ በአጎራባች ዞኖች ሰላምን ለማፅናት በሚሰጡት ግዳጆች ሚናውን በሚገባ እየተወጣ ያለ ሕዝባዊ ሠራዊት ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ ጽንፈኞች የሕዝቡን ሰላም ለማወክ በሞከሩ ጊዜ ቀድሞ በመድረስ የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ያፀና ሕዝባዊ ሠራዊቱ መኾኑን አስረድተዋል። ሚሊሻው በአንድ እጁ ልማትን በመከወን በሌላ እጁ ሰላምን የሚያረጋግጥ ኀይል መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፣ ሚሊሻው ለረጅም ዘመን የሠራው ጀብድ ትልቅ በመኾኑ ለዚህ ኀይል ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።

ሕዝባዊ ሠራዊቱ በቀጣይ ለሚሰጠው ማንኛውም ግዳጅ በጀግንነት ለመወጣት እራሱን ብቁ እንዲያደርግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።

በግዳጅ ወቅት ለተሰው የሚሊሻ እና ሰላም አስከባሪ ቤተሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ እና የገንዘብ ስጦታ ከተማ አሥተዳደሩ አበርክቷል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

#30ኛዓመት_ሚሊሻ #ከሚሴ #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚታዩ የግብርና ማነቆዎችን በመፍታት ምርትን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።