
ሁመራ: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሊጥ ምርት ድርሻ እና በውጭ ንግድ አቅርቦት የኢትዮጵያን 88 በመቶ ድርሻ የሚሸፍነው አማራ ክልል መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል። የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች በተገኙበት፤ የ2018/19 የመኸር ሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የውይይት መድረክ ከአልሚ ባለሃብቶች ጋር በሁመራ ከተማ ተካሂዷል።
ዞኑ ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ያለው ሲኾን ከዚህ መካከልም ከ189 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በባለሃብቶች እየለማ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ በመድረኩ ላይ ባቀረበው ሪፖርት አመላክቷል።
የዞኑን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ በተቻላቸው ልክ እየሠሩ መኾኑን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ዞኑ ያለውን የመልማት ጸጋ ተጠቅሞ ለማልማት የብድር አቅርቦት፣ የረዥም ጊዜ የመሬት ውል፣ በቂ የግብአት አቅርቦት አገልግሎት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
በአካባቢው በከፍተኛ መጠን የሚመረተውን የሰሊጥ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችል ኅብረት ሥራ ማኅበር እንዲቋቋምም ድጋፍ ጠይቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው፤ በዞኑና በአጎራባች ዞኖች የእርሻ መሬት ካዳስተር አለመሠራቱ መሬትን ለመቆጣጠር እንቅፋት መኾኑን ጠቁመዋል። ካዳስተር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም አቶ አሸተ አመላክተዋል።
አካባቢው በሰሊጥ፣ በማሾ፣ በጥጥና በሌሎች ሰብሎች ተጠቃሽ ከኾኑት የክልሉ አካባቢዎች አንዱ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ አንስተዋል።
በሰሊጥ የውጭ ንግድ አቅርቦትና በሀገራዊ ምርት ድርሻ አማራ ክልል 88 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን አቶ ደረጀ ገልጸዋል።
የዓለምን ነጻ የንግድ ውድድር በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የተነሳው ጥያቄ ተገቢ መኾኑን አንስተው ለዚህም የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ግብርናን ለማዘመን መንግሥት እና አልሚ ባለሃብቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አካቢው ሰፊ የግብርና ኢንቨስትመንት ቀጠና ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ላይ የሚገጥሙ ችግርን የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመፍታ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ባለሃብቶች እጃቸው ላይ ያለውን ነዳጅ ለተገቢው ዓላማ ብቻ እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
