
እንጅባራ: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የእጩዎች ትውውቅ እና የጎዳና ላይ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ በፓርቲው የተመዘገቡ ስኬቶችን የሚያሳዩ እና ለፓርቲው አጋርነትን የሚያንፀባርቁ መልዕክቶችም ተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ትበለጽጋለች፤ ብልጽግና ሀገርን ከብተና የታደገ ፓርቲ ነው፤ ብልጽግና የሀገር አንድነት እና የዜጎች ክብር ማረጋገጫ ፓርቲ ነው የሚሉ እና ሌሎችም መልዕክቶችም በሰልፈኞቹ ተስተጋብተዋል ።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል የመወሰን መብታቸውን በማረጋገጥ የእሳቤ እና የዕይታ ለውጥ ያመጣ ፓርቲ መኾኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ቀውሶችን በፅናት በማለፍ በኢኮኖሚው መስክ አበረታች ውጤት አስመዝግቧልም ነው ያሉት።
በእንጅባራ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት፣ የገበያ ማዕከል፣ የደም ባንክ እና ሌሎችም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ ትሩፋቶች እንደኾኑም አንስተዋል።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎችም ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና የተጀመሩ የልማት ውጥኖች ከዳር እንዲደርሱ ከፓርቲው ጋር እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይመራኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ በእጃቸው ይዘው የምርጫ ቀኑን በመጠባበቅ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ሰልፈኞቹ አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
