
ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ወጣቶች ባላቸው ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮው ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ ሀገርን እንደ መገንባት ይቆጠራል ብለዋል። ወጣቶች አባቶች ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር የመጠበቅ እና ለትውልድ የማስተላለፍ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት። ወጣቶች በመረጃ ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ በማድረግ ዜግነታዊ ግዴታቸውን በዕውቀት እና በምክንያታዊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሰላም አምባሳደር በመኾን የሰላም እንቅፋት የኾኑ ሐሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን መከላከል፣ ሕዝቡንም ከመደናገር መታደግ ይገባል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ በምርጫ ወጣቶች በምርጫ ምዝገባ ወቅት ሲያሳዩት የነበረውን ጠንካራ ተሳትፎ እስከ ምርጫው ማጠናቀቂያ ድረስ ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ ጥንቃቄ በማድረግ እና ቅንጅታዊ አሠራርን በመከተል ሊፈጠሩ የሚችሉ አላስፈላጊ ተግባራትን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት መቅደስ ኃይሉ ማኅበረሰቡ በእጁ ያለውን የምርጫ ካርድ ተጠቅሞ የሚወክለውን ፓርቲ እንዲመርጥ ግንዛቤ ለመፍጠር እና የሀሰት ወሬዎችን ለመከላከል ዝግጁ መኾኗን ገልጻለች። ሌላኛው ተሳታፊ ወጣት ነጋ መላክ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመታገል ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጧል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
