
ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚወስኑበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት ነው። ወጣቶች ደግሞ የዚህ ሂደት ንቁ እና ወሳኝ ተዋናይ ናቸው።
ወጣቶች የሰላም አምባሳደር በመኾን በሂደቱ ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ይገለጻል። ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና አሳታፊ እንዲኾን የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱም ይጠበቃል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት እና ለዘላቂ ሰላም እየሠሩ መኾናቸውን ለአሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ተናግረዋል።
ወጣት ቤተልሄም ቦሩ እንደገለጸችው ማኅበረሰቡ በዕውነተኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ምርጫውን እንዲያካሂድ ወጣቶች ኀላፊነታቸውን እየተወጡ ነው። የምርጫ ካርድ ከማውጣት ባለፈ በአካባቢያቸው ሰላምን የማስከበር፣ በአላስፈላጊ ወሬዎች አለመደናገር እና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ የምርጫ ሥርዓት እንዲከናወን የመሥራት ኀላፊነት የወጣቶች ነው ብላለች።
ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል ረገድ በንቃት በመሳተፍ ጥረት እያደረጉ ነው። ማኅበረሰቡ የምርጫ ካርድ እንዲያወጣ እና የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅ በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውን ገልጻለች።
ወጣት ሀብተማርያም የሻምበልም ሕዝቡ ያለምንም ፍርሃት እና ጭንቀት ምርጫውን እንዲያካሂድ አየሠሩ መኾኑን ነግሮናል። በያዙት የምርጫ ካርድ የሚፈልጉትን ፓርቲ እንዲመርጡ ግንዛቤ እየፈጠሩ መኾናቸውንም ገልጿል።
ወጣቶች ምርጫ ካርድ በመያዝ የራሳቸውን ዕድል የመወሰን መብታቸውን በምርጫ ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብሏል።
ወጣቶች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር እና ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በምርጫ ሂደቶች ላይ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህም የለውጥ ባለቤት፣ የሰላም አምባሳደር እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋልታ በመኾን ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግሯል።
መጭው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና አሳታፊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች በትጋት መሥራት ይገባቸዋል ነው ያለው።
በላቀ የሕዝብ ተሳትፎ ምርጫው እንዲሳካ በማድረግ ረገድ ወጣቶች በባለቤትነት መንፈስ እና በትጋት መሳተፍ እንዳለባቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
