
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 30ኛ ዓመት የሚሊሻ የምስረታ በዓል በሰሜን ሸዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አሥተዳደር ተከብሯል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ባስተላለፉት መልዕክት ሚሊሻው ለአማራ ሕዝብ በችግር ጊዜ ደራሽ ብርቅዬ የሕዝብ ልጅ መኾኑን በተግባር አስመስክሯል ነው ያሉት።
የሚሊሻ አባላቱ ከቤተሰባቸው እና ልጆቻቸው ጊዜ ቀንሰው ለሕዝብ ክብር እና ፍቅር ራሳቸውን የሰጡ ጀግኖች በመኾናቸው ታላቅ ክብር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የሚሊሻ ኀይል ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ለሀገር እና ለወገን ሰላም መከበር የከፈሉት ዋጋ ላቅ ያለ መኾኑን የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ገልጸዋል።
ሚሊሻው ከማኅበረሰቡ የወጣ እና ለማኅበረሰቡ የሚቆም የሰላም ምሰሶ መኾኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ በቀጣይም በጽናት እና በታማኝነት በመሥራት በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ ሚሊሻው በክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦት ለመቀልበስ በቁርጠኝነት መታገል እንደሚኖርበት አስገንዘበዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የሚሊሻ አባላት ንቁ ተሳታፎ በማድረግ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ ከፍተኛ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
