“ብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ ሰላም እንዲጸና ማድረግ ያስፈልጋል” አብዱ ሁሴን(ዶ.ር)

5

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በጉባላፍቶ ምርጫ ክልል በወልዲያ ከተማ አሥተዳደር የምርጫ ቅስቀሳ አድርገዋል።

የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ብልጽግና ፓርቲ አምራች አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪ በማገናኘት እድገትን ያፋጥናል ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት፣ በቤት ልማት አማራጮች፣ በኮሪደር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ልማቶችን በማስፋት፣ የሥራ እድል በመፍጠር ሕዝቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ቢሮ ኀላፊ እና የጉባላፍቶ ምርጫ ክልል እጩ ተወዳዳሪ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ብልጽግናን መምረጥ የሀገር ክብር እና ሉዓላዊነትን ማስቀጠል ነው ብለዋል። ዘመናዊ ከተማን በመፍጠር፣ የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት፣ የኢኮኖሚ ልማትን በማሳደግ ብልጽግና እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ብልጽግናን በመምረጥ የሀገርን ልማት ማስቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ብልጽግና በጠራ እሳቤ እየሠራ ያለ ፓርቲ መኾኑን አንስተዋል። የትናንት ችግሮችን እያከመ፣ የገባውን ቃል እየተገበረ እና ዛሬን ከነገ ጋር እያስተሳሰረ ያለ የተግባር ፓርቲ ነው ብለዋል።

የአርሶ አደሮች ሕይወት እንዲሻሻል፣ ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየሠራ የሚገኘውን ፓርቲ ግንቦት 24 በነቂስ በመውጣት መምረጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ብልጽግና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር በሠራው ሰፊ መሠረተ ልማት አማካኝነት ለሌሎች ሀገራትን እያስደመመ፣ የአፍሪካ ሀገራት እንዲነቃቁ እና ልምድ እንዲቀስሙ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የሀገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ የባሕር በር ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ብልጽግና የባሕር በር ጥያቄን በማስመለስ ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ነው ያሉት።

ብልጽግና የወልድያ ከተማን ከልማት እጦት በማራቅ ከተማዋን የሚመጥን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

ብልጽግናን በመምረጥ ሰላም እንዲጸና ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በማኅበራዊ፣ በዴሞክራሲያዊ እና በኢኮኖሚ ብልጽግናዋ የተከበረች እንድትኾን እንደ ስንዴ ነዶ አንድነት እንዲጸና ብልጽግናን ምረጡ ነው ያሉት።

የምግብ ሉዓላዊነታችንን የምናረጋግጠው በስንዴ ልማት በመኾኑ የስንዴ ነዶ ልትመርጡ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብልጽግና ፓርቲ መሪዎች እና አባላት በፍኖተ ሰላም ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።