“ምርጫ የሉዓላዊነት መገለጫ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

2

 

ደሴ: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ በኮምቦልቻ ከተማ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ እና ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎችን አስተዋውቋል።

በፕሮግራሙ የተሳተፉ የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሕይወት የሚቀይሩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል። በቀጣይም የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉ ድምጻቸውን ለፓርቲው ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉጌታ አቢ ብልጽግና ፓርቲ የዜጎችን ሕይወት የሚቀይሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት። በተለይ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እና ተስማሚ እንዲኾኑ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እያካሄደ መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትኾን እየተሠራ መኸኑንም ገልጸዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማ አሥተዳደሩ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ልማት እና እድገት ማስመዝገቡን አንስተዋል። ፓርቲው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የዜጎችን አብሮነት እያጠናከረ ይገኛልም ነው ያሉት። ፓርቲው ለሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ትኩረት በመሰጠቱ የዜጎችን ሕይወት የቀየሩ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ፓርቲው የጀመራቸውን የማልማት ሥራዎች ለማስቀጠል በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምርጫ የሉዓላዊነት መገለጫ መኾኑን ተናግረዋል።

በመኾኑም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ፓርቲው ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመጀመር እና በማጠናቀቅ ለትውልድ የሚሻገር ሥራ እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። ብልጽግና ፓርቲ በምግብ ራስን ለመቻል ለስንዴ ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ፓርቲው የጀመራቸውን ሥራዎች ከግብ ለማድረስ ዜጎች ድምጻቸውን እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

ፓርቲው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ኮምቦልቻ ከተማን እጩ ኾነው የቀረቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪዎችን አስተዋውቋል።

ዘጋቢ:- ሰይድ አብዱ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምርጫ የሥልጡን ሕዝብ መገለጫ ነው።
Next articleየብልጽግና ፓርቲ መሪዎች እና አባላት በፍኖተ ሰላም ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።