“ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ውስጥ 51 በመቶው ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

2

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች የታደሙበት የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ተካሂዷል።

በዚሁ መድረክ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ዓመታት ፓርቲው የገባውን ቃል በተግባር ሲያረጋግጥ መቆየቱን ገልጸው፤ በተለይም በሁሉም ዘርፎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መኾኑን አስረድተዋል።

ሴቶች በየደረጃው በአመራርነት እንዲሳተፉ ብቻ ሳይኾን፣ የአዲስ አበባን ቁልፍ ቢሮዎች በመምራት ረገድ ወሳኝ የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው መደረጉን ጠቁመዋል። ይህም ተሳትፎ ሴቶች መሥራት እና መለወጥ ስለሚችሉ የተሰጣቸው እንጂ ለይስሙላ እንዳልኾነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአምስት ዓመታት የለውጥ ጉዞ ውስጥ ሴቶች በሰላም እና ጸጥታ፣ በንግድ፣ በምክር ቤት እንዲሁም በታላላቅ የዲዛይን እና የግንባታ ሥራዎች ላይ ሙሉ ጊዜያቸውን በመሥጠት አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በተለይም እንደ ዓድዋ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለምርቃት እንዲበቁ የሴቶች ሚና የጎላ እንደነበርም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ውስጥ 51 በመቶው ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ መኾናቸውንም ከንቲባዋ ገልጸዋል። ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቀረቡ ዕጩዎች መካከል 54 በመቶው እንዲሁም በአዲስ አበባ ምክር ቤት 40 በመቶው ሴቶች መኾናቸው ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መኾኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፣ ሴቶች የብልጽግና ጉዞው ወሳኝ ባለቤቶች እና ባለድርሻዎች መኾናቸውን ገልጸዋል። በሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በማስወገድ፣ የሴቶችን የመቻል እና የመምራት አቅም ለሀገር ግንባታ እንዲውል ማድረግ መቻሉን በንግግራቸው አብራርተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዛሬ ወጣቶች ድምፅ የነገዋን ኢትዮጵያ እውን ያደርጋል።