
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ 06 መንደፈራ ቀበሌ ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት መርቀዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳ ውኃ እና ኢነርጅ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አድኖ ዋጋው የቀበሌው ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት በንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። የንጹሕ መጠጥ ውኃ ግንባታው ችግሩን እንደቀረፈም ተናግረዋል።
የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ በዋሽ ፕሮጀክት እና በክልሉ ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ድጋፍ መገንባቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከ12 ሺህ በላይ ሕዝብን ማስጠቀም እንደሚችልም ተናግረዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የቀበሌው የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር በብልጽግና ፓርቲ መፈታቱን ተናግረዋል።
በዞኑ 115 አነስተኛ የውኃ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን ነው የገለጹት። 10 ትላልቅ የውኃ ፕሮጀክቶችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ጠቁመዋል።
የውኃ ፕሮጀክቶቹ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እየተገነቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የብልጽግና ፓርቲ ቃሉን በተግባር በማረጋገጥ የሰሜን ወሎ ሕዝብን የልማት ጥያቄዎች እየመለሰ መኾኑን አንስተዋል።
ወረዳው በጦርነት የተጎዳ በመኾኑ መንግሥት ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመገንባት ተጠቃሚ እያደረገው ነው ብለዋል።
መንግሥት ባለፈው ምርጫ የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ ይገኛል ነው ያሉት። በቀጣይም ቃል የምንገባቸውን ሥራዎች እንፈጽማለን ብለዋል።
በወረዳው የማንጎ ክላስተር፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።
የግብርና ቴክኖሎጅዎችን በማቅረብ፤ የመስኖ ልማትን በማስፋት፤ አርሶ አደሮችን በቴክኖሎጅ ታግዞ እንዲያለሚ በማድረግ ብልጽግና ፓርቲ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።
“ፍጥነታችንን ያዘገዩት ይኾናል እንጅ ልማታችንን የሚስቆመን ኃይል የለም” ብለዋል።
ብልጽግና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኾኖ ለሕዝብ ብርሃን የሚያሳይ ፓርቲ መኾኑንም ተናግረዋል። ለኅብረ ብሔራዊነት፣ ለወንድማማችነት እና ለአንድ አፍሪካዊነት እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
