
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ የሰጡት አቅጣጫ ጽንፈኛውን ከገባበት ገብተው እንዲደመስስ የሞራል ስንቅ እንደኾናቸው የአንድ ክፍለ ጦር መሪዎች ተናግረዋል።
መሪዎቹ ዋና አዛዡ የሰጧቸው ግዳጆች የኅብረተሰቡን ሰላም የሚያረጋግጡ በመኾናቸው ለተግባራዊነታቸው ቀን ከሌት እንደሚተጉም አስታውቀዋል።
የክፍለ ጦር ዘመቻ ኀላፊ ሻለቃ አረጋዊ ገብረ መድኅን የክፍለ ጦራችን የበላይ አካል በሚሰጠን ማንኛውም ቀጣና በመግባት ግዳጃችን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
ለተልዕኳችን መሳካትም የእዛችን መሪ ግልጽ የኾነ የወደፊት አቅጣጫ ስለሰጡን እና ክፍለ ጦራችንን ማበረታታታቸው ለተወጣነው እና ቀጣይ ለምንወጣው ግዳጅ የሞራል ስንቅ ይኾነናል ብለዋል።
በክፍለ ጦሩ ስር የአንድ ሬጅመንት አዛዥ ሻምበል ካስየ አጥሌ የእዛቸው መሪዎች አቅጣጫ እስካሁን ለተወጡት አመርቂ የግዳጅ አፈጻጸም ወሳኝ እንደነበር ተናግረዋል። ጽንፈኛውን በማጽዳት አማራ ክልልን ወደ አስተማማኝ ሰላም ለመመለስ ቢሚያደርጉት የተቀናጀ ስምሪት የመሪዎች ድጋፍ እንዳልተለያቸው ተናግረዋል።
ከምሥራቅ እዝ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ምሥራቅ እዝ አሁን ላይ በጎጃም እና በደቡብ ጎንደር እያደረገ ባለው ዘመቻ ጽንፈኛው በሚገባ በመመታቱ ሕዝባችን መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶችን እያገኘ መጥቷል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
